ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገለፀ።

99

ባሕር ዳር: ጥር 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ንግድና ገበያ ልማት፤ ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጋር በመተባበር የዋጋ ንረትን መከላከልና መቆጣጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከንግዱ ማህበረሰብና ሸማቾች ጋር የውይይት መድረክ በከሚሴ ከተማ አካሂዷል።

አስተያየታቸውን የሰጡ የከሚሴ ከተማ ነዋሪዎች በከተማው እየተስተዋለ ያለው የዋጋ ንረት ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ገልፀዋል።

በከተማው በጤፍ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች በበኩላቸው፤ ለዋጋ ግሽበቱ ምክንያት የሆነው በአካባቢው የምርት እጥረት በመኖሩ ነው ብለዋል።
በአካባቢው የምርት እጥረት በመኖሩ ከሌላ ቦታ በውድ እንደሚረከቡ ገልጸዋል። ከሚረከቡበት አካባቢ መንግስት ጥብቅ ቁጥጥር ሊያደርግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አስተዳዳሪና የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ መሐመድ ሙሳ፤ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የተከሰተውን የሸቀጦች የዋጋ ንረት ለመከላከል ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከወረዳዎች ጋር በመተባበር ሥራዎችን እየሰራ ነው ብለዋል።

ለሕብረት ስራ ማሕበራት አምስት ሚሊዮን ብር በመደጎም ዘይት፣ ስኳርና ጤፍ ለህብረተሰቡ በቅናሽ ዋጋ እንዲቀርብ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

ኀላፊው አክለውም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብረሐይል በማቋቋም በተሠራው ሥራ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልፀው ይህ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሂም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleʺበላይ ዘለቀ- ጠላት የበረገገለት፣ ወገን የተመካበት”
Next article“ጃንሜዳን በህብረት ለጥምቀት” በሚል መሪ ቃል የታቦታቱን ማደሪያ የማፅዳት ስነስርዓት ተካሄደ።