ʺበላይ ዘለቀ- ጠላት የበረገገለት፣ ወገን የተመካበት”

202

ባሕር ዳር: ጥር 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገሩን ከአብራኩ ክፋይ አስበልጦ ወደዳት፣ ሀገሩን ከግራ ጎኑ አስቀዳማት፣ ሀገሩን ከወገን ዘመዶቹ አላቃት፣ ኢትዮጵያን በመከራ ውስጥ ኾኖ አፈቀራት፣ ለፍቅሯ ግለት በዱር በገደል ተመላለሰላት፣ በበረሃ ተንከራተተላት፣ ወንድም ገበረላት፣ ወዳጅ ዘመድ ሰጣት፣ የመከራውን ጽዋ ተጎነጨላት፤ ኢትዮጵያን ከሁሉም በላይ አስበለጣት፣ ከአንቺ በላይ የማስቀድመው የለኝም አላት፡፡

ኮልታፋ አንደበቷን እየሰማ ያሳደጋት፣ በእቅፉ ውስጥ አድርጎ ትንፋሽ የሰጣት፣ የልጅነት ማዕዛዋንም ያሸተታት፣ እየዳበሰ ልጄ ወዳጄ ያላት፣ ግንባሯን እየሳመ ታቲ ዝግራ ያጫወታት፣ እሾህ እንዳይወጋት፣ እንቅፋት እንዳይመታት የሳሳላት የሻሽወርቅን ከአንጀቱ ይወዳታል፣ ከዓይኑ ስትርቅ ይናፍቃታል፤ ከኢትዮጵያ ግን አላስበለጣትም፣ ኢትዮጵያን በልጁ አልተካትም፣ ሀገሩን በየሻሽወርቅ ለቅሶ ተክዞ ለጠላት አሳልፎ አልሰጣትም፡፡ የአባትነት ልቡን አበርትቶ፣ የሻሽወርቅን ትቶ ከሀገሩ ጠላቶች ጋር ተናነቀ እንጂ፡፡
በልጅ እና በእናት ሀገር ፍቅር ተፈተነ፡፡ ፈተናው ከባድ ነው፣ ልጅ እና እናት ሀገር ለምርጫ ቀርበዋል፡፡ የሚበልጠውን ማስቀደም ግድ ነበርና የሻሽወርቅን ትቶ ኢትዮጵያን አስቀደመ፡፡ ጠላት የበረገገለት፣ ወዳጅ የተመካበት አባ ኮስትር በላይ ዘለቀ፡፡

እረኞች በላይ በላይ እያሉ አዜሙለት፣ ባለቅኔዎች አባ ኮስትር እያሉ ተቀኙለት፡፡ እርሱ የተመላለሰባቸው ጋራና ሸንተረሮች፣ እርሱ ውጊያ የገጠመባቸው ምሽጎች አንደበት ቢኖራቸው በላይ በላይ ባሉ ነበር፡፡ ጠመንጃውን አንግቶ፣ ዝናሩን ሞልቶ፣ አፈሙዝ ወልውሎ፣ ሳንጃውን ስሎ ሲወጣ ሀገሩ ጉድ ይላል፤ ሁሉም በላይ በላይ ይላል፡፡

በዓድዋ ተራራ ላይ ዘመን የማይሽረው በትር ያረፈባት ኢጣሊያ የጣለችውን ክብሯን፣ ያጠፋችውን ስሟን መልሳ የምታነሳበት ዘመን ትጠብቅ ነበር፡፡ በእርሷ ላይ ያረፈው ብርቱ በትር ነጭን በመላ አስደንግጧል፣ ጥቁርን በመላ አኩርቷል፡፡ ምኒልክ በመሩት የዓድዋው ጦርነት ያረፈባት ምት በሮም የገነባችውን ገናናነቷን አፈራርሶታል፣ አጀብ የተሰኘውን የጦር ሜዳ ውሎዋን አጥፍቶባታል፣ ማንም አይችለው የተባለው ክንዷን አድቅቆባታል፤ አትጠልቅም ያለቻትን ጀንበሯን አጨልሞባታል፡፡

ኢጣሊያ በዓለም አደባባይ ያሳፈረቻትን ኢትዮጵያን ያለ በቀል ማለፍ አልተዋጠላትም፡፡ በቀደሙት መሪዎቿ በእነ አውግስቶስ ቄሳር፣ በእነ ኔሮ፣ በኋላም በዓድዋ ላይ የደረሰባትን ተደጋጋሚ ሽንፈት የምታካክስበት ሌላ ዕድል መሞከር አስፈለጋት፡፡ ኢትዮጵያን በክንዳቸው ደፍጥጠው እንዲያስገብሩ የተላኩት ወታደሮቿ ሁሉ በኢትዮጵያውን መዳፍ ተጨብጠው ቀርተዋል፡፡ በሮም አደባባይ ፎክረው የተነሱት በዓድዋ ተራራ ላይ እንዳልነበር ኾነዋል፡፡ ታዲያ ለዚህ ሁሉ በቀል አስፈለጋት፡፡

ኢጣሊያ በኢትዮጵያውያን ክንድ በዓድዋ ተራራ ላይ የደቀቀና የወደቀ ስሟን ታነሳ ዘንድ አርባ ዓመታትን ተሰናዳች፡፡ መሰናዶዋንም እንደጨረሰች ወደ ኢትዮጵያ ገሰገሰች፡፡ የዓድዋው ጀግና ምኒልክ አልፈው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በመንበሩ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ቂም የቋጠረችው ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ዳር ድንበር ማንዣበብ ጀመረች፡፡ ኢትዮጵያም ሉዓላዊነቴን እንዳትደፍሪ ስትል በጨዋ ደምብ ጠየቀች፡፡ ኢጣሊያ ግን አሻፈረን ብላ ወረራ ጀመረች፡፡ እንደ ዓድዋው ሁሉ በአጭር ጊዜ የሚቋጭ ጦርነት አልነበረም፡፡ ከባድ ጦርነት ተካሄደ፡፡ ለዓመታት የተዘጋጀችው ኢጣሊያ የኃይል ሚዛኗ ከፍ አለ፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ኃያል በደል አደረሰች፡፡
በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ ጀግኖች አርበኞች
ኧረ ጥራኝ ጫካው ኧረ ጥራኝ ዱሩ፣
ላንተም ይሻልሃል ብቻን ከማደሩ።
እያሉ በረሃ መውረድን፣ ከጠላት ጋር መዋደቅን አምርረው የጀመሩት፡፡ የኢጣሊያ ዘመናዊ መሳሪያ አስግቷቸው ሀገራቸውን አሳልፈው አልሰጡም፡፡ ሀገርን ለጠላት አሳልፎ መስጠት በኢትዮጵያውያን ዘንድ አይታወቅምና፡፡ ጀግኖች አርበኞች በየአቅጣጫው እየተነሱ ጠላትን መውጫ መግቢያ፣ ማለፊያ ማግደሚያ አሳጡት፡፡ በዚህ ዘመን በአርበኝነት ጠላትን ከቀጡ ጀግኖች መካከል ደጅ አዝማች በላይ ዘለቀ አባኮስትር ይነሳል፡፡ የበላይ አፈሙዝ የጠላትን ግንባር እየለየች መትታለች፣ የበላይ ጥይት ከጠላት ገላ እየተሰካች እልፍ ጠላትን ጥላለች፡፡

በላይ እንኳን በጦርነት በሰላምም ጊዜ ለሰላምታ ነጭ እጄን አይጨብጣትም የሚል ኩሩ ጀግና ነው፡፡ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር እነሆ ጀግና በሚለው መጽሐፋቸው ጄኔራል ሳንፎርድ የተባለ አንድ የእንግሊዝ መኮንን ለሰላምታ የበላይን እጅ ሊጨንጥ ሲዘረጋ በላይ ዘለቀ ʺለፈረንጅ እጄን አልሰጥም” አለው ብለዋል፡፡ እኔ የዘለቀ ልጅ እያለ ፍርሃት በልቡ ያልፈጠረበት ጀግና ለሀገሩ መከበር ያለ ድካም ከጠላት ጋር ተናንቋል፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ግዛቸው አንዳርጌ ( ረዳት ፕሮፌሰር) ኢትዮጵያ በትውልዶች ተከታታይነት ባለ ቆራጥነት ራሷን አስከብራ የኖረች ሀገር ናት ይላሉ፡፡ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ግዛቷን ለማስፋት የማታለልና እርስ በእርስ የማጣላት ሙከራዎችን አድርጋ አልሳካ ሲላት በጉልበት መጣች፡፡ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ የኢትዮጵያውያን ግፍና በደል ያንገበገባቸው፣ የሀገር ፍቅር ያቃጠላቸው ጀግኖች ለሀገር ፍቅር ተዋደቁ፡፡

ኢጣሊያ አዲስ አበባን እንደያዘች የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢጣሊያን መንግሥት እንዲያውቅ፣ የጦር መሳሪያ የያዙ እንዲያስረክቡና ግብር እንዲከፍል አዋጅ አስነገሩ ይላሉ ረዳት ፕሮፌሰሩ፡፡ የኢጣሊያ አዋጅ እንደተሰማም በርካታ ጀግኖችን አስቆጣ፣ በቁጣ ከተነሱት መካከልም በላይ ዘለቀ አንደኛው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በላይ በዘመኑ በነበረው መንግሥታዊ ሥርዓት አባቱ ሞቶበት ነበር፣ በደልም ደርሶበት ነበር፣ ዳሩ ጠላት ሲመጣ በስርዓቱ ተበድያለሁ እና ሀገሬን ጠላት ይውረራት አላለም፡፡ ለሀገሩ በጀግንነት ተነሳ እንጂ፡፡

አባ ኮስትር በላይ ልጁ የሻሽወርቅ በጠላት ተይዛ፣ ባለቤቱ አልፋ፣ የእርሱን ዘመዶች ቤት እያቀጠሉበት በላይ ግን ወደ ኋላ ሳይመለስ ይዋጋ ነበር፡፡ ጽናት፣ ጀግንነትና እመነት ከእርሱ ጋር ነበሩ፡፡ ጦርነቱ ለቀናት አልነበረም፣ ለሳምንታትም አልነበረም፣ ለወራትም አልነበረም፣ ለዓመታት ነው እንጂ፡፡ ለዓመታት በዘለቀው ጦር በላይ በጽናት የጠላት ግንባርን እየለየ መታ፡፡ የበላይ ዘለቀን ስሜት የሚነኩ አሳዛኝ ክስተቶች ተፈጥረዋል፣ በሸበል በረንታ የኢጣሊያ ወታደሮች ሕጻናትን እና ሴቶችን በግፍ ገድለዋል፤ ይሄን ሁሉ ያደረጉት በላይ ትግሉን እንዲያቆም ነበር፤ በላይ ግን የበለጠ ጸና፣ የበለጠ ጠነከረ እንጂ ነፍጡን አልዘቀዘቀም፡፡

ጣሊያኖች የሻሽወርቅን እንስጥህ እና ለእኛ እደር ብለውት ነበር፤ በላይ ግን ልጅም የሚኖረው በክብርም የሚኖረው ሀገር ሲኖር ብቻ ነው በማለት አሻፈረኝ አላቸው ይላሉ ረዳት ፕሮፌሰር ግዛቸው፡፡
ʺበላይ አባ ኮስትር በላይ አባ ነፍሶ፣
በረንታ ላይ ጣለው ለምጨን ላይ ተኩሶ” እየተባለ የተገጠመለት ተመልከት እያለ ጠላትን በየዱር ገደሉ የሚጥል፣ የጠላትን መሪ ከተመሪው ጋር በጥይት ብሎ የሚነጥል ጀግና ነው፡፡ የትኛውም ችግር ቢመጣ ተቋቁሞ የሀገር ፍቅር ማጽናትን፤ በጽናት፣ በጀግንነት፣ በውሳኔ ሰጭነት መቆምን በላይ ያስተምራልም ይላሉ፡፡ በላይ መከራውን ተቋቁሞ ለሀገር ዋጋ የከፈለ ጀግና ነው፡፡

የሕዝብን ሕልውና ለማስጠበቅ ከእነ በላይ ዘለቀ ታሪክ መማር ግድ ይላል የሚሉት ምሁሩ ሀገሩን የሚወድ ዜጋ የቀድሞ አባቶችን ታሪክ የሚያውቅ፣ የሚያከብር፣ ከአባቶቹ መልካም ሥራዎች ትምህርት የሚወስድ መኾን አለበት ነው የሚሉት፡፡ ታሪክን ማክበር ራስን መስከበር እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ ʺየጥሩ ዜጋ ምልክት የአባቶቹን ታሪክ የሚያከብር፣ ራሱንና ሀገሩን የሚያስከብር፣ ለወገኑ የሚቆረቆር፣ ሀገሩን የሚወድ ነው፡፡ የትኛውም ፈታኝ ሁኔታና ችግር ቢገጥም ከግለሰብ ችግር ይልቅ የሀገርን ችግር ማስቀደም፣ ለሀገርና ለሕዝብ ችግር ዋጋ መክፈል ይገባል” ነው ያሉት፡፡

ʺመኳንንቱ ሁሉ እየተጨነቀ፣
ለምጨን ካፋፉ ላይ ያው በላይ ዘለቀ፤
መኳንንቱ ሁሉ እምነቱን ሲያወልቀው፣
አባ ኮስትር በላይ አለ እንዳጠለቀው” እየተባለ የተገጠመለት ለሀገሩ ለገባት ቃል ኪዳን የኖረ፣ በሀገር ፍቅር የታሰረ ጀግና ነው በላይ ዘለቀ፡፡ በላይ አባ ኮስትር የኢጣሊያንን ሠራዊት እንደ ረመጥ ጠብሶ ሀገርን ነጻ አድርጓል፣ የሕዝብን ነጻነትም አስከብሯል፡፡ ዳሩ ከነጻነት ማግሥት በላይ ረጅም ዘመን አልቆዬም፡፡ ከንጉሣዊ ስርዓቱ ጋር አለመግባባት ተፈጠረ፡፡ ጎልማሳው በላይ ሮጦ ያልጠገበባትን፣ በእሳት ተፈትኖ ጀብዱ የሠራበትን፣ በሕይወቱ ተወራርዶ ነጻ ያደረጋትን ኢትዮጵያ ተሰናበታት፡፡ በላይ ከእነውነቱ፣ በላይ ከእነ ጀግንነቱ፣ በላይ ከእነ ነጻነቱ፣ በላይ ከእነ ልበ ሙሉነቱ ሳይጎድል ምድርን የተሰናበታት ልክ በዛሬዋ ቀን ጥር 5/1937ዓ.ም ነበር፡፡

የጀግና እድሜው ረጅም አይደለም የሚሉት ምሁሩ ጀግና ሰው በአጭር ጊዜ ዘመን የማይሽረው ታሪክ ይጻፋል ይላሉ፡፡ በላይን የፈጠረው የቀደመው የአባቶች ጀግንነት እንደነበርም ይናገራሉ፡፡ በአምስት ዓመቱ ለተገኘው ድል ከአርበኞቹ ጀርባ እረኞች፣ ስንቅ አቀባዮች፣ የቆሎ ተማሪዎች፣ አዝማሪዎች እና ሌሎች ተሳትፏቸው ከፍ ያለ ነበር፤ ታሪክ የጋራ ድምር ውጤት ነው ብለዋል ምሁሩ፡፡ እርስ በእርስ ከመባላት ትክክለኛውን ታሪክ በማስተማር መልካም ትውልድ መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬም የፀኑ አርበኞች እንደሚያስፈልጓትም አስገንዝበዋል፡፡

በምድር አጭር እድሜ የኖረው አባ ኮስትር ዘመን ተሸጋሪ ታሪክ ሠርቷል፣ ሀገርን በብርቱ ትግል በነጻነት አቆይቷል፣ ስሙን ከመቃብር በላይ ትቷል፡፡ ለሀገር ክብር ተዋድቀሃል፣ ለሀገር ክብር ደስታህን ትተሃል፣ ለሀገር ክብር የአብራክህን ክፋይ ረስተሃል፣ ለሀገርህ ክብር ቃል ኪዳንህን አጽንተሃልና ትውልድ በላይ በላይ ይለሃል፤ ስምህን እየጠራ ይምል ይገዘትብሃል፤ አባ ኮስትር ኾይ አፈሩ ይቅለልህ፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አባል ነን በሚሉ አጭበርባሪ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ተወሰደ።
Next articleከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገለፀ።