ʺፍየል በጉ ታርዶ ተጥሎ ፍሪዳ ያውቅበታል ጎንደር ሲቀበል እንግዳ”

177

ባሕር ዳር: ጥር 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እንግዳ መቀበል ታውቅበታለች፣ ስሞት አፈር ስኾን እያለች ታቃመጥላለች፣ ብሉልኝ ጠጡልኝ እያለች እንግዶቿን ታሞናሙናለች፡፡ ለእንግዶቿ ጃኖውን ትደርባለች፣ ካባውን ታለብሳለች፣ ከጠጁ እየቀዳች፣ ከፍርንዱሱ እየሞላች ታጠጣለች፣ ከጮማው እየቆረጠች ታጎርሳለች፣ ታሪክና ሃይማኖት፣ እሴትና ጀግንነት ታስተምራለች፡፡

እንግዶች ይወዷታል፣ መዳረሻቸው ያደርጓታል፣ ታሪክና ጥበብን ያዩ ዘንድ ይጓዙባታል፣ በደረሱም ጊዜ በፍቅርና በክብር ይቆዩባታል፡፡ በዘመናቸው የማይረሱት ትዝታ፣ ከፍ ያለም እርካታ ይዘው ይመለሱባታል፤ ለምን የከበረው ታሪኳን፣ የረቀቀው ሃይማኖቷን፣ የሀገር ዋልታነቷን ያዩባታል፣ ይማሩባታልና፡፡

ʺፍየል በጉ ታርዶ ተጥሎ ፍሪዳ
ያውቅበታል ጎንደር ሲቀበል እንግዳ” እንደተባለ ጎንደር ፍሪዳውን ጥላ እልፍኙን አሰማምራ እንግዳ መቀበሉን ታውቅበታለች፡፡

ባሕሏን ትጠብቃለች፣ ሀገር የምትታወቅበትን፣ ሕዝብ የሚኮራበትን፣ ትውልድ የሚመካበትን ባሕል ትጠብቃለች፣ ለልጅ ልጅ ታስተላልፋለች፣ ወንዶች አበው ባጌጡበት ያጌጣሉ፣ ሴቶች እናቶች በተዋቡበት ይደምቃሉ፤ ወንዶች እንደ አባቶቻቸው ጃኖውን ይለብሳሉ፣ ጎራዴና ጋሻውን ይታጠቃሉ፣ እንደ በረዶ የነጣውን ሸማ ይደርባሉ፡፡

ሴቶች በሀገሬው ሸማኔ የተሸመነውን፣ የሴትነት ውበትን የሚያጎላውን፣ በሚያምር ጥበብ የተሸሞነሞነውን ቀሚስ ያጠልቃሉ፡፡ በቀጭን ወገባቸው ላይ መቀነታቸውን ሸብ ያደርጋሉ፣ እንደ እናቶቻቸው ሹርባውን ተሰርተው፣ በአልቦና በድሪው ተውበው ይወጣሉ፡፡

የጥንቱን የሚያኮራውን እና ወግ ፤ባሕሉን የጠበቀውን ይይዛሉ፡፡ የእናትና የአባቶቻቸውን ቃል ኪዳን ያከብራሉ፣ ባሕልና ወጋቸውን ከታሪክና ከማንነት ጋር አስተሳስረው ይዘው ይኖራሉ፡፡

ጎንደር ፣ሃይማኖትን፣ ታሪክን፣ አንድነትን፣ ባሕልን፣ ወግ እና ሥርዓትን ይዛለች፡፡ በታሪኳ ግዝፈት ስሟን ከፍ አድርጋ ስታስጠራ ትኖራለች፣ በዓለ ጥምቀቱ ደርሷል፣ ድግሡ ተደግሷል፡፡ እልፍኙ ተሰናድቷል፤ ቤተ መንግሥቱ በክብርና በኩራት ተውቧል፡፡

ʺየአጼ ቴዎድሮስ ሀገር ደግሞም የፋሲል
ከወዴት ይገኛል አንቺን የሚመስል” እያሉ አዝማሪዎች እያሽሞነሞኗት፣ እያወደሱና እያሞገሷት ጎንደር ተውባ ተሰናድታለች፡፡

በጥምቀተ ባሕሩ ሃይማኖት፣ ጀግንነት ፣ ታማኝነት፣ አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት እና አርቆ አሳቢነት የተጠመቀች፣ በቃል ኪዳን የፀናች፣ በጀግኖች የተጠበቀች፣ አልሞ የሚተኩስ፣ ፈትፍቶ የሚያጎርስ፣ አውልቆ የሚያለብስ፣ መከራን አሻግሮ፤ ከደስታ የሚያደርስ ሕዝብ ያለባት-ጎንደር ለእንግዶቿ ላማረው በዓል ተውባለች፤ ያላዩዋት ያዩዋት ዘንድ የሚመኟት ሙሽሪት ጎንደር፡፡ ቀድማ የከተመች፣ አስቀድማ የዘመነች፣ የስልጣኔ አውታር የኾነች፣ ትናንት እና ዛሬን አጣምራ የያዘች ናት።

በሰሞነ በዓለ ጥምቀት የጎንደር ጎዳናዎች የሀገርኛ ልብስ በለበሱ ውቦች ይደምቃሉ፡፡ በጎዳናዎቿ የሚመላለሱ እንግዶች ከነዋሪዎች ጋር በፍቅርና በአንድነት ይመላለሳሉ፣ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ሥፍራዎችን ያስሳሉ፡፡ በጎንደር ከጥምቀት በዓል አስቀድሞ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ዝግጅቶች አሉ፡፡ እነዚህ ዝግጅቶችም ወደ ጎንደር ለሚያቀኑ እንግዶች ተጨማሪ መዳረሻዎች፣ ለከተማዋም ተጨማሪ ውበቶች ናቸው፡፡ ከጥምቀት በዓል አስቀድሞ የባሕል ሳምንት ዝግጅት በጎንደር ከተማ ይሰናዳል፡፡ በበዓል ሳምንቱም በርካታ ሁነቶች ይካሄዳሉ፡፡ ዘንድሮም ይሄው የባሕል ሳምንት ይደረጋል፡፡

የጎንደር ዓለም አቀፍ ቅርሶች አሥተዳደሪ ጌታሁን ስዩም፤ ጥምቀት በጎንደር ሲከበር ከሌሎች አካባቢዎች ለዬት ብሎ ይከበራል ይላሉ፡፡ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ እንደተጠበቀ ኾኖ ባሕላዊ ክዋኔዎች በዓሉን የበለጠ ያደምቁታል፡፡ ጎንደር ለበዓለ ጥምቀት ከረጅም ወራት ጀምራ ዝግጅት እንደምታደርግም ነግረውኛል፡፡

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ የባሕል እሴት ኢንዱስትሪ ቡድን መሪ ልዕልና አበበ፤ ጥምቀት በጎንደር ሃይማኖቱን እና ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ይከበራል ነው ያሉት፡፡ ጎንደር በዓሉን ስታከብር ሃይማኖቱን እና ትውፊቱን ጠብቃና አክብራ ነውም ብለዋል፡፡ ባሕል በበዓላት ወቅት ከሌላው ጊዜ በበለጠ ይንጸባረቃልም ነው ያሉት፡፡

በባሕል ሳምንቱ የአካባቢውን ወግና ሥርዓት የሚያሳዩ አለባበሶች፣ አጨፋፈሮች እንዲጸባረቁ ይደረጋል፡፡ በበዓል ሳምንቱ ልዩ ልዩ ባሕላዊ ክዋኔዎች ይደረጋሉም ተብሏል፡፡ የጎዳና ላይ ትርዒቶች፣ ባሕላዊ ክዋኔዎች ሳምንቱን የሚያደምቁት ናቸው፡፡ የባሕል ሳምንቱ ሲከበር አለባበስ፣ አመጋገብ፣ ሥራ ወዳድነት፣ ጀግንነት፣ እንግዳ ተቀባይነትን፣ አንድነትን፣ ሀገር ወዳድነትን በሚያንጸባርቅ መልኩ ይኾናል፡፡

በዘንድሮው የባሕል ሳምንት ከአማራ ክልል ከሁሉም አካባቢዎች የተውጣጡ የአዝማሪዎች ፌስቲቫልም ይካሄዳል፡፡ ዓለም አጫዋቾች ከነገሥታቱ፣ ከመኳንንቱ፣ ከመሳፍንቱ፣ ከሊቃውንቱ፣ ከጦር አበጋዞች እና ከሌሎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት በሚያሳይ መልኩም ይከበራል፡፡ አዝማሪዎቹ በጥበባቸው ነገን ያሳያሉ፣ ወታደሩን ያጀግናሉ፣ ንጉሡና ንግሥቷን ከሕዝቡ ጋር በአንድ ላይ ያስደስታሉ፡፡ ይሄን ሲያደርጉ የኖሩ አዝማሪዎችን የሚዘክር አሁን ያሉትን የሚያከብር በዓል ነው የሚደረገው፡፡

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ቻላቸው ዳኘው ጎንደር የባሕል፣ የታሪክ እና የኀይማኖት ባለቤት ናት ብለዋል፡፡ ጥምቀት በጎንደር እጅግ ተውቦ ይከበራል፤ የጎንደር ሕዝብ እንግዳ ተቀባይና በሀገሩ የማይደራደር መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ከጥምቀት በፊት ያለው ሳምንት “የባሕል ሳምንት” ብለን እናከብረዋለንም ነው ያሉት፡፡

በጎንደር ከጥምቀት በዓል በተጨማሪ የታሪክ እና የባሕል ሁነቶች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡ ግጥምን በማሲንቆ እና ሌሎች ሁነቶችም በጥምቀት መዳረሻ በጎንደር ይከወናሉ ብለዋል፡፡ ጎንደርን በበዓለ ጥምቀቱ እና ከዚያ አስቀድሞ ባሉ ቀናት ጎንደርን ማየት ልዩ ደስታ እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጥምቀትን በኢራንቡቲ!
Next articleሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አባል ነን በሚሉ አጭበርባሪ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ተወሰደ።