
የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ በደብረ ማርቆስ የደም ባንክ አገልግሎት ተገኝተው ዛሬ ጠዋት ደም ለግሰዋል።
በደም እጥረት ምክንያት የሚቀጠፈውን ሕይወት ለመታደግ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ኅብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ ደም በመለገሱ ርዕሰ መሥተዳድሩ አመሥግነዋል።
በመኪና አደጋ፣ በወሊደና ሌሎች ምክንያቶች በደም እጥረት ሕይወታቸውን የሚያጡ ወገኖችን ደም በመለገስ መታደግ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድር ተመሥገን አሳስበዋል፡፡
በሌሎች አካባቢዎች እንደሚታዬው የሕዝብን ሕይወት አደጋ ላይ በሚጥሉ እኩይ ተግባራት ከመሳተፍ ይልቅ የሰውን ልጅ ሕይወት ሊጠብቁ በሚችሉ በጎ ተግባራት ላይ ሕዝቡ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ በደም ልገሳው የታየውን መተባበር የክልሉን ሠላም እና ልማት በሚያጠናክሩ ተግባራት መድገም እንደሚገባም አቶ ተመሥገን ጠይቀዋል።
የደብረ ማርቆስ ደም ባንክ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ከፋለ ገበየሁ በምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች ሥር በሚገኙ 14 ሆስፒሎችና የጤና ተቋማት ደም እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፤ በክረምቱ ትምህርት ሲዘጋ የደም አቅርቦት እጥረት እንደሚያጋጥምም ተናግረዋል፡፡ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በቦታው በመገኘትና ደም በመለገስ ያሳዩት አርዓያነት ለሌሎች አስተማሪ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ትናንት ጥቅምት 15 ቀን 2012ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በነበረው የደም ማሰባሰብ መርሀ ግብር በደብረ ማርቆስና አካባቢው 250 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ከ320 ዩኒት በላይ ደም መሰብሰቡንም ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
በተለያዩ አጋጣሚዎች ደም የሚያስፈልጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች እያጋጠሙ በመሆናቸው ኅብረተሰቡ ንቁ ተሳት ሊያደርግ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ትናንት ጥቅምት 15/2012 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀምበር 10 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ እንደነበር ይታወሳል። ከ11 ሺህ ዩኒት በላይ ደም እንደተሰበሰበም የጤና ሚኒስቴር አስታወቋል፡፡
መረጃውን ያደረሱን ጋሻዬ ጌታሁን እና ተመስገን ዳረጎት ናቸው።