
ባሕርዳር: ጥር 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “የሃይማኖት አብሮነት ለዘላቂ ሰላም እና ለሁለንተናዊ ትብብር” በሚል መሪ መልዕክት የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጎንደር ከተማ መክሯል፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንዳሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ በሚያገለግሉ ሰባኪ ግለሰቦች ምክንያት በአንዳንድ ሃይማኖት ተቋማት መካከል ጤናማ ያልኾነ የፉክክር መንፈስ እየተንፀባረቀ ነው።
እነዚህ ግለሰቦች በየቤተ እምነቶቻቸዉ የሚሰብኩት ስብከት የሌሎች እምነት እና አስተምህሮን በመተቸት ፣በማንኳሰስና ክብረ ነክ የኾኑ ይዘቶችን ከቤተ እምነት መድረኮቻቸዉ አልፈዉ በቴሌቪዥን ጣቢያዎች እና በማኅበራዊ ሚዲያ ጭምር በመታገዝ ለብዙኃኑ ሲያሰራጩ ተመልክተናል ብለዋል።
ይህ አይነቱ ድርጊት መንፈሳዊነት የጎደለዉ ብቻ ሳይኾን በዓለማዊውም ሕይወት ተቀባይነት የለውም ብለዋል። በመኾኑም ይህን መሰል ፀብ አጫሪ ስብከቶች ሊታረሙ ይገባል ነው ያሉት።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዘውዱ ማለደ እንዳሉት የጎንደርን ሰላም የማይፈልጉ አካላት ከዚህ ቀደም በሃይማኖት ሽፋን ሁከት እና ብጥብጥ ለማስነሳት ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። ለዚህም የሃይማኖት አባቶች እና ሰላም ወዳዱ የጎንደር ሕዝብ ለሠራዉ ሥራ ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- አዲስ ዓለማየው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!