“ሁል ጊዜም በምንከፍለው ዋጋ ሀገር እናስቀጥላለን” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

271

ባሕር ዳር: ጥር 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኤታመዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በባሕርዳር በሚገኘው የሰሜን ምዕራብ እዝ ደረጃ ሦስት ሆስፒታል ተገኝተው የሠራዊት አባላትንና ባለሙያዎችን ለፈጸሙት ጀግንነት አበረታትተዋል። ከጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊውጂን ጨምሮ ከፍተኛ የጦር ጄኔራል መኮንኖች ተገኝተዋል።

የሰሜን ምዕራብ እዝ ደረጃ ሦስት ሆስፒታል አዛዥ ኮሎኔል እንየው አያሌው ሆስፒታሉ ለሁሉም እዞች ድጋፍ ሲያደርግ የቆዬ መኾኑን ተናግረዋል። በጀግንነት ሲዋጉ ጉዳት የሚደርስባቸው ጀግኖችን በመጠበቅና በመንከባከብ አኩሪ ሥራ ሠርቷልም ብለዋል። የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ሠራዊቱን በማበረታታታቸው ለሌላ ግዳጅ እንዲነሳሱ ያደርጋልም ነው ያሉት።

የመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ ኀላፊ ሌተናል ጄኔራል ጥጋቡ ይልማ የሰሜን ምእራብ እዝ ደረጃ ሦስት ሆስፒታል በጦርነቱ ወቅት ውጤታማ አገልግሎት መስጠት የቻለ ከፍተኛ ተቋም መኾኑን ተናግረዋል። ጠንካራ ድጋፍ ሰጪ የግንባር ሆስፒታል እንደኾነም አስረድተዋል። ለተቋሙ ውጤታማነት የመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ መምሪያ፣ የአማራ ክልል ፣ የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር፣ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች ተቋማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ነው የገለጹት።

የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የሠራዊት አባላቱን ባበረታቱበት ወቅት ሠራዊቱ ለሁለት ዓመታት ሀገርን ለማዳን መስዋዕት ከፍሏል ፣ሕይወቱን ገብሯል ብለዋል። በጦርነት መቁሰል፣ መድማት፣ መሞት አለ፣ መስዋዕትነት እየከፈሉ ሀገር ጠብቆ ይኖራል ነው ያሉት።

አባቶቻችን መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው ሀገርን ለእኛ ያቆዩልንም ብለዋል። ሁል ጊዜም ለሀገር እንዋጋለን እንቆስላለን፣ እንሰዋለን፣ ሀገር እናስቀጥላለን ነው ያሉት ኤታማዦር ሹሙ። ለሀገር መስዋዕትነት መክፈል የነበረና የቆዬ መኾኑንም አንስተዋል። እናንተ ባትቆስሉ ኖሮ ዛሬ ላይ እዚህ መገናኘት አንችልም ፣ሀገራችን ችግር ውስጥ ትገባ ነበር ፣እናንተ ቆስላችሁ ሀገር እድናችኋል ፣ታሪክ ሠርታችኋል ፣የአባቶቻችሁን ታሪክ ደግማችኋል ብለዋቸዋል።

በእናንተ መሰዋእትነት ሀገር ቆማለች ሕዝብ ኮርቷል ነው ያሉት። ለሀገሩ መስዋዕትነት የከፈለውን ሠራዊት ሀገር ትንከባከበዋለች ፣ትጠብቃዋለች ብለዋል። እናንተ በከፈላችሁት ዋጋ ሰላም መጥቷልም ብለዋቸዋል።

የሰሜን ምዕራብ እዝ ደረጃ ሦስት ሆስፒታል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ገልጸዋል። በወቅቱ ማዕከል ኾኖ ማገልገሉንም ተናግረዋል። የመከላከያ ዋና ጤና መምሪያ በጦርነቱ ወቅት የድርሻውን በከፍተኛ ብቃት በመወጣቱ ምስጋና ይገበዋልም ብለዋል። ከመከላከያ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ተነሳሽነት መከላከያውን በከፍተኛ ደረጃ ደግፈዋልም ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ለ28 ሆስፒታሎች በቅደመ ክፍያ ውል መድኃኒቶችን ሊያቀርብ ነው
Next article“የሌሎች እምነት እና አስተምህሮን በማንኳሰስ የሚቀርቡ ስብከቶች ሊታረሙ ይገባል” የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ