
ባሕርዳር: ጥር 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ለ28 ሆስፒታሎች በቅደመ ክፍያ ውል መድኃኒቶችን ሊያቀርብ መኾኑን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ውል የተገባለት የመድኃኒት አቅርቦት ሥርዓት ትግበራ የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ከ28 ሆስፒታሎች ጋር አካሄደ።
አገልግሎቱ ከሆስፒታሎቹ ጋር ውል የገባው ፍላጎትን መሠረት ባደረገ የአሠራር ሥረዓት ነው።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ፤ የተጀመረው የአሠራር ሥርዓት በኢትዮጵያ የሚታየውን የመድኃኒት አቅርቦት ችግር 80 በመቶ የሚፈታ መኾኑን ገልጸዋል።
አገልግሎቱ በተለይ 150 የሕይወት አድንና ሌሎች መድኃኒቶችን ለ28 ሆስፒታሎች በቅደመ ክፍያ ውል ለማቅረብ ከስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
በዚህም የአሠራር ሥርዓት ቢያንስ 95 በመቶ የአቅርቦት ፍላግትን ተደራሽ ለማድረግ ግብ እንደተጣለ አስታውቀዋል።
ከዚህም በተጨመሪ በሙከራ ደረጃ ሲሠራበት የቆየው የፈጣን ለውጥ አምጪ እቅድ ሥርዓትን በሆስፒታሎች የሚጀመር መኾኑ ገልጸዋል።
በጤና ፕሮግራም የሚሰጡ የቲቢ፣ የኤች አይ ቪ፣ የወባና እና የክትባት መድኃኒቶች በመሠረታዊ መድኃኒት የአሰራር ስርዓቱ ላይ እንዲዘረጉ ይደረጋል ብለዋል።
መድሃኒቶቹንም በየአስራ አምስት ቀኑ ለየሆስፒታሎቹ እንደሚያቀርብም አስርድተዋል።
በአጠቃላይ በአገልግሎቱ የተገዙ መድኃኒቶችን ውል ለገቡ ሆስፒታሎች የማድረስ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ኢዜአ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!