የአማራ ሕንፃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ለቀጣይ ሥራው ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ከአጋር አካላት ጋር መከረ፡፡

84

ባሕርዳር፡ ጥር 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሕንፃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት በሀገሪቱ የተፈጠረውን የዋጋ ንረት እና የአቅርቦት እጥረት ችግር ለመፍታት ከአቅራቢ ድርጅቶችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል።

የምክክሩ ዓላማ አዳዲስ አቅራቢዎችን ለመጋበዝና ያሉ ችግሮችን ተነጋግሮ ለማስተካከል ያለመ ነውም ተብሏል።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ታደሰ ግርማ፤ የአማራ ሕንፃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የመንግሥትን ክፍተት ለመሙላት እና በሀገሪቱ የልማት ጉዞ የድርሻውን አስተዋጽኦ ለማድረግ የተቋቋመ ድርጅት ነው ብለዋል፡፡

ድርጅቱ ባለፉት ዓመታት በአማራ ክልልም ኾነ በሀገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች በርካታ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን፣ የሆስፒታል ግንባታዎችን፣ የትምህርት ቤት ግንባታዎችን ፣የአስፓልት መንገድ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱንም ተናግረዋል።

የድርጅቱ የሕንፃ ተገጣጣሚ ፋብሪካ እና ተሽከርካሪዎችን፤ ለመስኖ አገልግሎት የሚውሉ ፕላስቲኮችን በማምረት በሀገሪቱ የልማት ተሳትፎ ኀላፊነቱን እየተወጣ እንደኾነም አቶ ታደሰ አስረድተዋል።

ድርጅቱ በቀጣይ የሥራ ጉዞ የሚገጥሙትን ችግሮች ከአጋር አካላት ጋር በመወያየት ለመፍታት ታሳቢ ያደረገ ምክክርም ማካሄዱ አስፈላጊ እንደኾነ ነው የገለጹት።

በምክክሩ የሕንፃ ግንባታ እቃዎች ግብዓት ዋጋ እየጨመረ መምጣት እና የሥራ አፈፃፀም ክፍተቶች መኖር ሥራዎችን በተቀላጠፈ መንገድ ለማከናወን ችግር መኾኑ ተነስቷል። ድርጅቱ የገጠሙትን ችግሮች ገምግሞ በቀጣይ ሥራው ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር መዘጋጀቱም ተመላክቷል።

ባለድርሻ አካላቱ የጋራ ክፍተቶች መኖራቸውን አንስተው በቀጣይ በጋራ ለመሥራት ከስምምነት ደርሰዋል።

ዘጋቢ፡- አየለ መስፍን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በግማሽ ዓመቱ 33 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰብስበናል” ኢትዮ ቴሌኮም
Next article“በክልሉ ለሚያለሙ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎች እንዲኖሩ እንሠራለን” ርእሰ መሥተዳደር ይልቃል ከፋለ