
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 15/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ይማሩ የነበሩና ባለፈው ዓመት በፀጥታ ችግር ምክንያት የሁለተኛ ወሰነ ትምህርት ማጠቃለያ ፈተና ያልወሰዱ የአማራ ክልል ተማሪዎችን ዩኒቨርሲቲው ለአንድ ዓመት አግዶ እንደመለሳቸው ተማሪዎች መግለጻቸውንና የዩኒቨርሲቲውን ምላሽ መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡
ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው በባሕር ዳር በሕዝብ ድጋፍ ስንቅና ማረፊያ ሲቀርብላቸው የቆዩ 93 ተማሪዎች ዛሬ ወደየቤተሰባቸው መመለሳቸውን የተማሪዎቹን የኅብረተሰብ ድጋፍ ሲያስተባብር የነበረው የባሕር ዳር አማራ ወጣቶች ማኅበር ሰብሳቢ ሄኖክ ሀብቴ ተናግሯል፡፡
ተማሪዎቹ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የተላፈው ውሳኔ ተገቢ አለመሆኑን ለአማራ ክልል መንግሥት ቅሬታቸውን ለማሰማት ወደ ባሕር ዳር መጥተው ነበር፤ በባሕር ዳር ከተማ ወጣቶችና ነዋሪዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው ጥያቄዎቻቸውን ለመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሲያቀርቡም ሰንብተዋል፡፡ ለጥያቄያቸው የክልሉ መንግሥት የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግረው ምላሽ እስኪሰጧቸው ድረስ ተማሪዎቹ ዛሬ ወደየቤተሰቦቻቸው መሸኘታቸውን ነው የባሕር ዳር አማራ ወጣቶች ማኅበር ሰብሳቢ ሄኖክ ሀብቴ ለአብመድ የተናገረው፡፡
በባሕር ዳር ሰፈነ ሠላም ወጣት ማዕከል እንዲያርፉ ተደርጎ ወደሚፈልጓቸው ተቋማት በወጣቶች እገዛ ሲሄዱ የነበሩት ተማሪዎቹ ዛሬ ጠዋት በባሕር ዳር ከተማ የጽዳት ሥራ አከናውነው እኩለ ቀን ላይ ወደየአካባቢያቸው ተሸኝተዋል፡፡
ተማሪዎቹ ከጎጃምና ጎንደር አካባቢዎች የመጡ እንደነበሩ ያስታወሰው ሄኖክ ከባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በተውጣጣ ገንዘብ መኪና እስከተገኘበት የመጓጓዣ እንደተከፈለላቸውና መኪና ወዳልተገኘባቸው አካባቢዎች ደግሞ ለመጓጓዣ የሚሆን ገንዘብ እንደተሰጣቸው ተናግሯል፡፡
የተማሪዎቹ ጉዳይ በኮሚቴ እየታዬ መሆኑንና ውጤቱ ለተማሪዎቹ ወደፊት እንደሚገለጽላቸው መነገሩን ያስታወቀው ሄኖክ ‹‹በባሕር ዳር የቆዩት 93 ተማሪዎች ዛሬ ወደ ቤተሰብ ተሸኝተዋል፤ አጠቃላይ ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ የተሰናበቱት ተማሪዎች ቁጥር ግን ከ560 በላይ ናቸው›› ብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት