ማኅበረሰቡን እየፈተነ ያለው የውኃ ችግር!

114

ባሕርዳር: ጥር 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግር የሚዳ ወረሞ ሬማ ከተማ ነዋሪዎችን እየፈተነ ነው።

ሬማ ከተማ በሰሜን ሸዋ ዞን ሚዳ ወረሞ ወረዳ የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ናት።የከተማዋን የውኃ ችግር ለመቅረፍ በ2009 ዓ.ም በ50 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የውኃ ተቋም ባጋጠመው ችግር ማኅበረሰቡ ለውኃ ችግር መጋለጡን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ነግረውናል። የውኃ ችግሩ በተለይም ደግሞ በተማሪዎች ላይ የጎላ መኾኑን ተማሪ ሐውለት መሐመድ ነግራናለች። ተማሪ ሀውለት እንደነገረችን ለከተማዋ ነዋሪዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተገነባው የውኃ ፕሮጀክት ችግሩን ይቅርፋል የሚል ተስፋ ተጥሎበት ነበር።

ይሁን እንጅ ፕሮጀክቱ ተስፋ በተጣለበት ልክ አገልግሎት ባለመስጠቱ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሷል። አልፎ አልፎ በሚደረግለት ጥገና በተለቀቀ ቀን ውኃ ለማግኘት የሚደረደረው ጀሪካን ቁጥር ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው።

አብዛኛው ሰውም ወረፋ ሳይደርሰው ወደ ወንዝና ጉድጓድ ውኃ ለመቅዳት ይጓዛል። የጉድጓድና የወንዝ ዳር ምንጭ ውኃ ለማግኘት ደግሞ ከአምስት ሰዓት በላይ ወረፋ ለመጠበቅ ይገደዳሉ።

ውኃ ለመቅዳት በሚወስደው ጊዜ ሁለትና ሦስት የትምህርት ክፍለ ጊዜዎችን አሳልፋ ክፍል እንደምትገባ ነው የነገረችን። የውኃ ችግሩ በተማሪዎች እያሳደረ ያለውን ጫና ተማሪ ሐውለትን ለአብነት አነሳን እንጅ በከተማዋ ማኅበረሰብ ላይም መከሰቱን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ነግረውናል።

የሚዳ ወረሞ ወረዳ ውኃና ኢነርጅ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰጠኝ እንችፉ የውኃ ፕሮጀክቱ ምንጭና የምንጩ ውኃ የሚጠራቀምበት የመጀመሪያ ታንከር በክረምት ወራት በጃራ ወንዝ ደለል እንደሚሞላ ነግረውናል። ወረዳውም የጎርፍ መከላከልና አቅጣጫ የማስቀየር ሥራ ቢሠራም ከወንዙ ግዙፍነት አኳያ ችግሩን መከላከል አልተቻለም።

ከመነሻ ታንከሩ ወደ ከተማው የተዘረጋው የውኃ ቱቦም ጥራታቸው ያልጠበቁና የተለያየ መጠን ያላቸው በመኾኑ በየጊዜው ለብልሽት ይዳረጋሉ። በዚህም የሚገፋው ውኃ ወደ ኋላ እንደሚመለስም ነው የነገሩን። በእነዚህ ምክንያቶች ማኅበረሰቡ እስከ ሦስት ወር ውኃ የማያገኝበት ጊዜ እንደሚከሰት አንስተዋል። ችግሩን ለክልሉ ውኃ ቢሮ አቅርበው “በጀት እያፈላለግን ነው” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት ትኩረት እንዲሰጠውም ጠይቀዋል።

. የሬማ ከተማ የንጹሕ መጠጥ ውኃ በ2006 ዓ.ም ተጀምሮ 2009 ዓ.ም የተጠናቀቀ ፕሮጀክት ነው።
. ፕሮጀክቱ 50 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጎበታል።
. በወቅቱ ለ12 ሺህ ሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ ታሳቢ ተደርጎ ነበር የተገነባው።

የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጅ ቢሮ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ዳይሬክተር ኤፍሬም ምኒሽር ባለፈው ዓመት በ700 ሺህ ብር ወጪ ወደ ታንከሩ ውኃ እንዳይገባ የወንዝ መግራት ሥራ በጊዜያዊነት መሠራቱን ገልጸዋል። ይሁን እንጅ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የንጹህ መጠጥ መነሻ ምንጭ የኾነውን የጃራ ወንዝ ለመከተር ወይንም ለመግራት ከፍተኛ በጀት እንደሚጠይቅ ነው ያነሱት። ወንዙ ካለው ስፋትና ግዙፍነት አኳያ በአጭር ጊዜ የሚሠራ ሳይኾን ጊዜ ወስዶ የማልማትና ፍጥነቱን የመቀነስ ሥራ ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት በጀት እንዳጸደቀ ወደ ሥራ እንደሚገባ ነው የገለጹት ።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለወልድያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የሕክምና መሣሪያዎች ድጋፍ ተደረገ።
Next articleየጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በባሕርዳር ተገኝተው የሰሜን ምዕራብ እዝን እየጎበኙ ነው።