
ባሕርዳር: ጥር 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰበት የወልድያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ30 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ የሕክምና መሣሪያዎች ድጋፍ ተደረገ፡፡
ድጋፉ የተደረገው በሂውማን ብሪጅ ግብረሰናይ ድርጅት አማካኝነት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በድጋፍ ርክክቡ ላይ የጤናው ዘርፍ በግጭቱ ምክንያት ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰበት ገልጸዋል፡፡
የተደረገው ድጋፍ ያጋጠሙትን ችግሮች በመቅረፍ የተሟላ የቀዶ ጥገና፣ የምርመራ እንዲሁም ለጨቅላ ሕፃናት አገልግሎት በተሟላ መልኩ ለመስጠት እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት የሂውማን ብሪጅ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር አዳሙ አንለይ ድርጅቱ ዛሬ ከተደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ለሌሎች ጉዳት ለደረሰባቸው ተቋማት ድጋፍ አድርጓል ማለታቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!