“የመጨረሻው ‘ወይዘሪት ቱሪዝም- አማራየቁንጅና ውድድር’ በጎንደር ከተማ ይካሄዳል ” የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ

301

ባሕርዳር፡ ጥር 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ለማነቃቃት የሚያስችልሉ ዘርፈ ብዙ ዝግጅቶች መደረጋቸውን የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው አበበ እንቢአለ ለአሚኮ ኦንላይን ተናግረዋል።

አቶ አበበ እንዳሉት በክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ለማነቃቃት ከሚያስችሉ ፕሮግራሞች መካከል በአይነቱ የተለየና የመጀመሪያም የኾነ “ወይዘሪት ቱሪዝም- አማራ “የቁንጅና ውድድር ነው የተዘጋጀው።

ይህ የቁንጅና ውድድር ፕሮግራም አዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደርን ጨምሮ በአማራ ክልል ከሁሉም ዞኖች የተውጣጡ ቆነጃጅቶች ተሳትፈውበታል ብለዋል።

ውድድሩ ሂደቶችን አልፎ አሁን ላይ ለመጨረሻው “ወይዘሪት ቱሪዝም- አማራ” አሸናፊነት ተወዳዳሪዎች እለቱን እየጠበቁ እንደኾነም ተናግረዋል።

የመጨረሻው ውድድር ጥር 7 ቀን 2015 ዓ.ም በጎንደር ከተማ አጼ ፋሲል ቤተመንግስት ውስጥ ነው የሚካሄደው ብለዋል።

የጥንት ጎንደሪያን ዘመንን መነሻ አድርጎ ቦታው እንደተመረጠ የገለጹት አቶ አበበ፤ የዚያን ዘመን ነገስታት የቁንጅና ውድድርን በመናገሸዋ ጎንደር ያካሂዱ ነበርና ያን ለማስታወስ ታስቦ የተመረጠ ነው ብለዋል።

የመጨረሻውን ውድድር አሸናፊዋ ቆንጆ የ2015 ዓ.ም የዓመቱ “ወይዘሪት ቱሪዝም- አማራ” የክልሉ የባህል አምባሳደር በመኾንም ትሰየማለች።
ለቀጣይ አንድ ዓመትም የአማራን ወግ ፣ባህልና አኗኗር በማስተዋወቅ የአምባሳደርነት ሚናዋንም ትወጣለች። በየዞኑ አሸናፊ ኾነው የተወዳደሩት ደግሞ የየመጡበት ዞን አምባሳደር ይኾናሉ ነው ያሉት።

በተያያዘም ቢሮው ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው “የድንቅ ምድር እውቅናና ሽልማት” ፕሮግራምም በጎንደር ከተማ ይካሄዳል።

ድንቅ ምድር- የእውቅናና ሽልማት ፕሮግራም በ41 የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ሥራዋች ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላት የምስጋና፣ አውቅናና ሽልማት የሚሰጥበት ነው ብለዋል አቶ አበበ።

ፕሮግራሙ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀ ሲኾን በየዓመቱም የሚቀጥል ይኾናል ። እውቅናውን የሚያገኙት ከግለሰብ እስከ ቡድንና ተቋማትን የሚያካትት እንደኾነ ነው የተገለጸው።
– ድንቅ ሁነት አዘጋጆች፣
– ደንቅ የስፖርት ከተሞች፣
– ድንቅ የቱሪዝም መዳረሻ ያላቸው ቦታዎች፣
– ድንቅ ሀገራዊ ኮንፈረስን የሚያስተናግዱ ከተሞች፣
– ድንቅ የማኅበረሰብ አቀፍ የቱሪዝም አካባቢዎች፣
– ለቱሪዝም ልማትና አንቅስቃሴ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላት፣
– የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ፣
– የእደጥበብ ሥራ፣
– የሆቴልና መስተንግዶ አገልግሎት… እና ሌሎችም እውቅናና ሽልማት ከሚበረከትላቸው የባህልና ቱሪዝም ዘርፎች ተጠቃሾች ናቸው ።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ባንኮች ለመክፈት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ ገለፀ።
Next articleለወልድያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የሕክምና መሣሪያዎች ድጋፍ ተደረገ።