
ባሕርዳር፡ ጥር 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በመከላከያ ሚኒስቴር ሥር በሚገኙ የተለያዩ ዘርፎችና ተቋማት ባለፉት ሥድስት ወራት የተከናወኑት ተግባራት አበረታች መኾናቸውን አብረሃም በላይ (ዶ.ር) አስታውቀዋል፡፡
የመከላከያ ሚኒስቴር በሥሩ ከሚገኙ ክፍሎች ጋር የሥድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሩ አብረሃም በላይ (ዶ.ር) በግምገማው ላይ እንደገለጹት፤ በሚኒስቴሩ ሥር የሚገኙ ክፍሎችና ተቋማት የሚሰጣቸውን የሥራ አቅጣጫ ተቀብለው በትክክል እየተገበሩ ነው፡፡
የመከላከያ ኢንጂነሪንግ፣ ፋይናንስ ዘርፍ፣ የመከላከያ ውጭ ግንኙነት ጥናት እና ምርምር ማዕከል እንዲሁም ሌሎች ተቋማት ችግር ፈቺ ሥራዎቻቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚኒስትሩ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
የመከላከያ የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ትክክለኛ የመከላከያን እና የኢትዮጵያን ክብር ያስጠበቀ እንዲሁም የተቋሙን እውነተኛ የሰላም ጉዞ ለዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ማሳወቁ እንዲጠናከር ዶክተር አብረሃም አሳስበዋል፡፡
በቢሾፍቱ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው አርሚ ሪፈራል ሆስፒታል በአጭር ግዜ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ አቅጣጫ መቀመጡን የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ያላክታል፡፡
የመከላከያ ጥናትና ምርምር ማዕከል የሚያከናውናቸው የሥራ ተግባራት ወቅትን የጠበቁ የምርምር ሥራዎች መሆናቸን ገልጸው፤ በሕግ ማስከበር ዘመቻ በዓይነትና በገንዘብ የተደረጉ ድጋፎችን ሰንዶ ለታሪክ ማስቀመጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!