
ደብረማርቆስ: ጥር 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ታሪክ ለማወቅ የጎጃም ገዥዎችን ታሪክ መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡ የጎጃም ሀገረ ገዥዎች ታሪክ የሚጀምረው ከደጃዝማች ዮሴዴቅ (1744 – 1749) እንደኾነ በርካታ የታሪክ ፀሐፊዎች ዘግበውታል፡፡
ዮሴዴቅ በዳግማዊ ኢያሱ ብርሃን ሰገድ (1664-1699) ዘመን ለማዕከላዊ መንግሥት አልገብርም ብሎ ከማስቸገር አልፎ እስከ ጨጨሆ በር ድረስ እየጋለበ ለጎንደር ቤተ መንግሥት ስጋት ፈጥሮ እንደነበር አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራን በመጥቀስ ዶ.ር ሥርግው ገላው ጽፈዋል፡፡ ኢያሱም የዮሴዴቅን ኀያልነት ካየ በኋላ ቀልብ ሊይዝ የእናቱን ልጅ ዳግማዊት ወለተ እስራኤልን ዳረለት፡፡ (አለቃ ተክለ ኢየሱስ፣2008፡20)
ወለተ እስራኤል የእቴጌ ምንትዋብ ልጅ ናቸው፡፡ “ቋረኛዋና ጥሩይቱ እቴጌ ምንትዋብ የአፄ ባካፋ ባለቤት በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያን ለሰላሳ ዓመት አስተዳድረዋል፡፡ አፄ ባካፋ በወጣትነታቸው ሰለሞቱ ከሁለቱ የተወለደው ቀጣዩ ንጉሥ ኢያሱ ዓለም ሰገድ ነግሦ እቴጌ ምንትዋብ በሞግዚትነት መንግሥቱን ያስተዳድሩ ነበር፡፡ እቴጌ ምንትዋብም ወጣት ሰለነበሩ ከምልምል ኢያሱ ሦስት የሚያማምሩ ልጆችን ወለዱ፡፡ ”(ጥላሁን ብርሃን፣2008፡33)
እነሱም ወለተ እስራኤል፣ አስቴርና አልጣሽ ናቸው፡፡ ምንትዋብ ሴት ልጆቿን ለታዋቂ ኢትዮጵያውያን መሳፍንት በመዳር ግዛቷንና የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር ተጠቅማባቸዋለች። ወለተ እስራኤልን ለጎጃሙ ገዥ ደጃዝማች ዮሴዴቅ ተድራ ኃይሉን ወልዳለች፡፡ (አለቃ ተክለ ኢየሱስ፣2008፡22) የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የዘር ሀረግም የሚመዘዘው ከዚህ ትውልድ ነው፡፡ ዮሴዴቅ ታላቅ ኃይሉን ይወልዳል፣ ታላቅ ኃይሉ መርድን እና ድንቅነሽን ይወልዳሉ፣ ድንቅነሽ የዳሞቱን ባላባት ደጃዝማች ዘውዴ ስልን አግብተው ደጃዝማች ጎሹን ወለዱ፣ደጃዝማች ጎሹ ዘውዴ ደግሞ ደጃዝማች ተሰማን፣ ደጃዝማች ብሩን፣ ደጃዝማች ንጉሴን፣ ልጅ ይማምን ይወልዳሉ፡፡ ደጃዝማች ተሰማ ጎሹ ራስ አዳልን (ንጉሥ ተክለ ሀይማኖትን) ወለዱ፡፡ራስ አዳል (ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት) ደግሞ የተሰማ ጎሹ ልጅ ነው፡፡
ልጅ አዳል የእናቱ ሀገር በደብረ ኤልያስ ወረዳ ገነት አቦ ነው፡፡ ፊት ትቤ አቦ ይባልም ነበር፡፡ የልጅ አዳል እናት ወይዘሮ ምዕላድ ነገዷ ከአፄ እስክንድር የማርታ፣ የቴዎድሮስ፣ የዓመተ ክርስቶስ፣ የዕርቄ፣ የኢዮልያ፣ የቱፋ፣ በቋ ልጅ ናት፡፡ (አለቃ ተክለኢየሱስ፣2008፡219). ልጅ አዳል በሕፃንነቱ አያቱ ጎሹ በካሳ ኃይሉ (አፄ ቴዎድሮስ) ከተገደሉበትና አባቱ ተሰማ ጎሹ ከተጋዘ በኋላ ዘመድ የጭንቅ ዕለት ነውና በአባቱ አደራ ባይነት ወደ አጎቱ ተድላ ጓሉ የቀድሞዋ መንቆረር ያሁኗ ደብረ ማርቆስ ተልኮ ከልጆቹ ከንጉሴና ከደስታ ጋር እየተማሩ አደጉ፡፡
ከዚያ በኋላ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የጎጃም ገዥ ለመሆን ብዙ ፈተናዎችን አልፈዋል፡፡ በቀድሞዋ መንቆረር በአሁኗ ደብረ ማርቆስ የሚገኘዉ የጎጃም ገዥዎች ቤተመንግሥት በ1845 ዓ.ም ደጃዝማች ካሳ (ዳግማዊ ቴዎድሮስ) የጎጃምን ግዛት ለማደላደል ዘመቻ አድርገው ክረምት በ1845 መንቆረር (አሁን ደብረ ማርቆስ) ውስጥ ቤተ መንግሥቱ በሚገኝበት ቦታ የሳር ሰቀላ ቤቶችን አሰርተው መክረማቸውና በቦታውም ከተማ እንዲቆረቆር ትዕዛዝ ሰለማስተላለፋቸው የቤተመንግሥቱ ጅማሬም ለደጃዝማች ካሳ እና ለደጃዝማች ተሰማ ጎሹ/የንጉስ ተክለሃይማኖት አባት/ መካረሚያ ከተሠሩ ጎጆች እንደኾነ ይነገራል፡፡ ደጃች ተድላ ጓሉ (1847-1860)፣ ደጃች ንጉሴ ተድላ(1860)፣ ደጃዝማች ደስታ ተድላ(1860-1861) እንደ ሁኔታው ጎጃምን ሲገዙ ቆይተውበታል፡፡
ከደጃዝማች ደስታ ተድላ በኋላ ጎጃምን የገዙት ራስ አዳል ተሰማ (ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት) በዘመናቸው የቤተ መንግሥቱን የውስጥ አደረጃጀት በማስፋፋት የአስተዳደር ሥራ በተደራጀ መንገድ እንዲከናወን በመደረጉና በሳር ክዳን ሰፊና ትልቅ አዳራሽ አሠርተው ሰለነበር በአካባቢው ማኅበረሰብ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ቤተ መንግሥት በሚል ስያሜ መጠራት እንደጀመረ ይነገራል፡፡ ሥያሜው ከንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በኋላም ሳይለወጥ አሁን ላይ ደርሷል፡፡ ራስ አዳል ተሰማ በአጼ ዮሐንስ ዘመነ መንግስት ጥር 13 ቀን 1873 ዓ.ም በደብረ ታቦር ከተማ ላይ ‹‹ንጉሠ ከፋ ወጎጃም›› ተብለዉ የሸዋው ንጉስ ምኒሊክ በተገኙበት ነገሡ (ተክለጻድቅ፣200፡59)፡፡
አለቃ ተክለ ኢየሱስ ራስ አዳል ተሰማ ከንግሥና በኋላ ያከናወኗቸውን ተግባራት እንዲህ ዘግበውታል፡፡“ንጉሥ ተክለ ሃይማት በጎጃምና በከፋ ነግሦ ከመጣ በኋላ በጎጃምና በዳሞት ሹም ሽር አደረገ፡፡ የበኩር ልጁን በዳሞት ራስ በዛብህ አሰኘ፤ ቀጥሎ ደግሞ በአፄ ዩሐንስ ፈቃድ ጎጃምን በመንቆረር በዘና ታቦተ ማርቆስን ተክሎ ደበረ፡፡ ብዙ ቅፈፍ አግብቶ 318 ደብተራ ሰራለት፡፡ መልዕልተ አድባር (ከአድባራት በላይ) ይሁን አለ፡፡ ደብረ ማርቆስ ይባል እንጅ መንቆረር አይባል ብሎ አዋጅ ነገረ፡፡ አለቃ መልአከ ፀሐይ መሸሻን፣ ሊቀ ጠበብት ጽሐፌ ትዕዛዝ እሸቴን ሾመ፡፡ ለጥንት ባለአፈሮችም ለመንቆረርና ለዝና ልጆች የዣባጢን የጮቢ የሚባል ሀገር ምንጣፍ ተክቶ ሲሶ ግብዝና ለርሱ፣ ሁለት እጅ ለጥንት ባለአፈሮች ሰጠ፡፡” (የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ገጽ 263)
ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ራስ እያሉ ጀምሮ ከጎጃም የስልጣን ተቀናቃኞቻቸው ጋር እና ከኢትዮጵያ ነገሥታት ጋር በርካታ ጦርነቶችን አካሂደዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሀገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ሁለት ታላላቅ ዘመቻዎችን አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው የሱዳን ደርቡሾች ድንበር ተሻግረው ጎንደር ድረስ በመግባት ጥር 10 ቀን 1880 ዓ.ም ቤተክርስቲያን አቃጥለው ቀሳውስቱን ሲገሉ እንዲህ ተብሎ ተገጠመ፡-
ተከተልኸኝ ብየ ዞሬ ዞሬ ሳይ፣
ወይ ጥጋብ ወይ ኩራት ጎንደር ቀረህ ወይ?
ወገራ አሳላፊ ደንቢያ እንጀራ ጣይ፣
ተበላህ ጎንደሬ አተትነሳም ወይ?
በወቅቱ አጼ ዮሐንስ አስመራ ስለነበሩ ይህንን በቀል ንጉስ ተክለ ሃይማኖት እንዲበቀል መልዕክት በመላካቸው ንጉስ ተክለ ሃይማኖት አንድ መቶ ሺህ የሚኾን ሰራዊታቸውን ይዘው በመሄድ ድል አድርገዋል ምንም እንኳን በሁለተኛው ዘመቻ ወቅት ቢሸነፉም (ተክለጻድቅ፣2000፡6)፡፡ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት በር በከፈተው ታላቁ የአድዋ ጦርነት ወቅትም የጎጃምን ጦር በመምራት ሦስት ሺህ ሰራዊት ይዘው በመዝመት ታላቅ ድል አስመዝግበዋል። (ተክለጻድቅ፣2000፡109፤)፡፡
የግዛት ዘመናቸውም ራስ አዳል ተሰማ ተብለው ከ1861-1872 ዓ.ም ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ተብለው ከ1873-1893 ዓ.ም ለ32 ዓመት ጎጃምን ገዝተዋል፡፡ በዘመናቸው የተሻለ ነው ብለው ያሰቡትን ነገር ለራሳቸውና ለሀገራቸው ሲፈጽሙ ኑረው ጥር 3 ቀን 1893 ዓ.ም በእለተ አርብ ደብረ ወርቅ ላይ አረፉ፡፡ እነኾ የጎጃም መገለጫ የኾኑት ሀገር ወዳዱ ታላቅ ንጉስ ካረፉ ዛሬ 122 ዓመታቸዉ ነዉ፡፡ ሁሌም በየዓመቱ ጥር 3 ቀን እሳቸዉ በመሰረቱትና አጽማቸዉ በሚገኝበት መልዕልተ አድባር ደብረ ጸሃይ ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስትያን መታሰቢያ ይደረግላቸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- መልሰው ቸርነት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!