ʺሙሽራዋ ተሞሽራለች፣ እልፍኙንም አስውበዋለች”

124

ባሕር ዳር: ጥር 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር ዋልታዋ ተሞሽራለች፣ የሀገር አለኝታዋ ተሞሽራለች፣ የጀግኖች እናት ተሞሽራለች፣ የጥበባት አምባ ተሞሽራለች፣ የታሪክ ብራናዋ ተሞሽራለች፣ የምስጢር ባለቤቷ ተሞሽራለች፡፡ እልፍኙ ተውቧል፣ ቤተ መንግሥቱ አምሯል፡፡ ዙሪያ ገባው አጊጧል፡፡

ነገሥታቱ ያማረውን ቤተ መንግሥት አነፁባት፣ የዙፋናቸው መቀመጫ አደረጓት፣ በትረ መንግሥቱን ጨብጠው፣ አስፈሪውን ዘውድ ጭነው ተመላለሱባት፣ ከመኳንንቱ እና ከመሳፍንቱ ጋር እየመከሩ ሀገር አጸኑባት፣ አንድነትን አተሙባት፣ ዘመን የማይሽረውን፣ ትውልድ የማይረሳውን ታሪክ ጻፉባት፡፡ ነገሥታቱ በፊት በኋላቸው፣ በግራ በቀኛቸው ታጅበው፣ ባማሩ ፈረሶች፣ በሚያምር ሰረገላ ተቀምጠው፣ እልል እየተባለላቸው፣ ሕዝቡ እጅ እየነሳቸው፣ ምርቃቱና ኾታው እያጀባቸው ኖሩባት፡፡ ሊቃውንቱ እንደ ውኃ ፈለቁባት፣ ምስጢር አመሴጠሩባት፣ ጥበብን ገለጡባት፣ ደቀመዛሙርቱ እውቀትን ገበዩባት፡፡

ወይዛዝርቱ ያማረውን ለብሰው፣ የተዋበውን ሹርባ ተሰርተው፣ በአልቦና በስንድዱ ተውበው በቤተ መንግሥቱ አጸድ ሥር ኖረውባታል፣ በጎዳናዎቿ ተመላልሰውባታል፣ ይመላለሱበታል፡፡ ጎበዛዝቱ ጎራዴያቸውን ታጥቀው፣ ጋሻቸውን አስተካክለው፣ ጦራቸውን አሹለው በኩራትና በክብር በቤተ መንግሥቱ ይታያሉ፤ ዙሪያ ገባውን በተጠንቀቅ ይጠብቃሉ፣ ሀገራቸውን ከጠላት ይከላከላሉ፡፡

ድንቅ ውበት ተችሯታል፣ ባለዜማዎች ያዜሙላታል፣ ባለ ቅኔዎች ይቀኙባታል፣ ዓይኖች ሁሉ ይመለከቷታል፣ ቁጥራቸው የበዛ ጎብኚዎች ታሪኳን ለመረዳት፣ ውበቷን ለማዬት ይጓዙባታል፡፡ ያማሩ አብያተ መንግሥታት፣ የተዋቡ አብያተክርስቲያናት፣ የበዙ ታሪካዊና መንፈሳዊ ቅርሶች ባለቤት ናት ሙሽራዋ ጎንደር፡፡

እጅግ በተዋበው ቤተ መንግሥት አጸድ ሥር ኢትዮጵያዊነት ጸንቶበታል፣ አንድነት በርትቷል፣ የሀገር ፍቅር ከፍ ከፍ ብሎበታል፡፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ በኩራትና በክብር ተውለብልቦበታል፣ እነኾ ዛሬም አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ በታላቁ ቤተ መንግሥት አናት ላይ በክብር ይውለበለባል፡፡ ጎንደር ለሀገር ዋልታና ማገር የኾነች፣ በኢትዮጵያዊነት ልክ የኖረች፣ ኢትዮጵያዊነትን አክብራ ያስከበረች፣ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ከፍ ያደረገች ናት፡፡ አበው ጎንደር በታሪክ የከበረች ራሷም ታሪክ የኾነች ከተማ ናት ይሏታል፡፡

ጎንደር በሰርክ የፈጣሪ ስም ይጠራባታል፣ ኪዳን ይደረስባታል፣ ቅዳሴ ይቀደስባታል፣ ምስጋና እና ውዳሴ ይቀርብባታል፣ ጸሎትና ምስጋና አይቋረጥባትም፣ ጎበዝና ገበዝ አይታጣባትም፡፡ ሩቅ ተጓዥ ነጋዴዎች ግመሎቻቸውን፣ ፈረስና በቅሎዎቻቸውን እየጫኑ ሩቅ ተጉዘው መጥተው ከትመውበታል፣ ነግደው አትርፈውበታል፣ በደስታና በፍቅርም ኖረውበታል፡፡

አሰግድ ተስፋዬ ጎንደር የአፍሪካ መናገሻ በሚለው መጽሐፋቸው የዜና መዋዕል ጸሐፊ አዛዥ ሲኖዳን ጠቅሰው ጎንደርን ሲገልፁ ʺ በአህጉሩ ላመል ምንም የማይታጣባት” ብለዋታል፡፡ አበው ጎንደርን የአፍሪካ መናገሻ፣ የስልጣኔ አምባም ይሏታል፡፡ አሰግድ ሞንሩ ሃይን ጠቅሰው ሲጽፉ ደግሞ ʺ የገነት አምሳያ የጥቁር ሕዝቦች ማማʺ ብለዋታል፡፡ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ ሀገር አሳሾች፣ ባለ ቅኔዎች ጎንደርን አሞግሰዋታል፣ አድንቀዋታል፡፡ የማድነቂያ ቃል አጥተውላት ሁልጊዜ አዲስ፣ ሁልጊዜ ሙሽራ ይሏታል፡፡

የጎንደር ከተማ የግል አስጎብኚዎች ማኅበር ሊቀመንበርና አስጎብኚ ፋንታሁን ያለው ጎንደር እድሜ ጠገብ ከተማ ናት ይላታል፡፡ ጎንደር አጼ ፋሲል ከመንገሳቸው፣ ታላቁን ቤተ መንግሥትም ከማሠራታቸው አስቀድማ የነበረች ከተማ ሳትኾን እንዳልቀረች የሚጠቁሙ ታሪኮች አሉ ይላል፡፡ ስሟ ከፍ ከፍ ያለው ግን አጼ ፋሲል መናገሻቸው ካደረጓትና ግዙፉን ቤተ መንግሥት ከገነቡባት በኋላ ነው፡፡

ጎንደር ጠቢባን፣ ዘማሪያን፣ ጀግኖች፣ ነጋዴዎችና ሌሎች በአንድ ላይ የኖሩባት፣ የሚኖሩባት ታላቅ ከተማ ናት፡፡ ታላቁ ንጉሥ አጼ ፋሲል በሁለት አፍላጋት መካከል ባለ፣ በተራራ በተከበበ፣ ለዙፋን መቀመጫ በተመቻቸ፣ እጅግ በተዋበ ሥፍራ ላይ ቤተ መንግሥታቸውን ሠሩ፡፡ ቤተመንግሥታቸውም እስከዛሬ ድረስ ንጉሡ ዘውዳቸውን ጭነው፣ ካባቸውን ደርበው፣ በትረ መንግሥታቸውን ጨብጠው፣ በመኳንንቱና በመሳፍንቱ ተከበው፣ ከባለቤታቸው ጋር ተቀምጠው የሚኖሩበት፣ የጦር አበጋዞች የሚመላለሱበት፣ ቤተ መንግሥቱን በኩራትና በክብር የሚጠብቁት ይመስላል፤ ግርማው አልቀነሰም፣ አስፍሪነቱን አልተነጠቀምና፡፡

ንጉሠ ነገሥት ፋሲል መናገሻቸው ባደረጓት ከተማቸው ቤተ መንግሥት ብቻ ሳይኾን፣ አብያተ ክርስቲያናትን፣ የሹማምንት እና የመኳንንት ቤቶችን፣ ድልድዮችን እና ሌሎች ያማሩ ኪነሕንጻዎችን ሠርተዋል፡፡ የፋሲል መናገሻ ጎንደር ሊቃውንት የሚሰባሰቡባት፣ የበቁ አባቶች የሚኖሩባት፣ ጥበብ የሚፈልቅባት፣ ታማኝ እና ኩሩ የሚገኝባት ናት፡፡

ታላቁ ንጉሥ ፋሲል አልፈው ሌሎች ነገሥታት በነገሡ ጊዜም በታላቁ ቤተ መንግሥት አጸድ ሥር አብያተ መንግሥታትን አሠርተዋል፤ የማሩ ኪነ ሕንጻዎችን አስገንብተዋል፣ አድባራትን ደብረዋል፡፡ በቀደመው ዘመን የጎንደር አብያተ መንግሥታት የግቢ ሥፋት አሁን ከሚገኙበት በሁለት እና በሦስት እጥፍ ይበለጥ እንደነበርም ፋንታሁን ነግሮኛል፡፡ በቀደመው ዘመን የጎንደር አብያተ መንግሥታት ከሃያ ሥድስት የማያንሱ በሮች እንደነበሩትም ፈንታሁን ይናገራል፡፡ አሁን ላይ በተዋበው ቤተ መንግሥት ዙሪያ አሥራ ሁለት በሮች አሉ፡፡ አራት ድልድዮችም በቤተ መንግሥቱ ዙሪያ ይገኛሉ፡፡ እነኚህ ድልድዮች ሕዝብ ሠርቷቸው እየተጓዘባቸው ነገሥታቱ በታላቅ አጀብ የሚያልፉባቸው የነበሩ ናቸው፡፡ ዛሬም የትናንቱን ታሪክ እየዘከሩና እየመሰከሩ አሉ፡፡

የጎንደር ነገሥታት ክንፍ ቀረሽ መልአክ እየተባሉ የሚወደሱና የሚሞገሱ ነበሩ፡፡ ለምን የረቀቀና የተዋበውን ነገር አድርገዋል፣ እጹብ ድንቅ የሚያሰኘውን ነገር ሠርተዋል፣ ከፍ ከፍ ብለው ተረማምደዋልና፡፡ ነገሥታቱ ከቤተ መንግሥት ወጥተው ለኪዳን እና ለቅዳሴ ወደ አብያተ ክርስቲያናት ሲወጡ፣ ወደሌሎች ዝግጅቶችም ሲኼዱ ባሰሩት ድልድይ አልፈው ወደ ፈለጉበት ሥፍራ ይሄዱ ነበር ይላል ፋንታሁን፡፡ ይሄም ጥበባቸው ሲያስደንቃቸው እና ሲያስሞግሳቸው ይኖራል፡፡

እጅግ በረቀቀ ጥበብ በተገነባው፣ በከበረው ቤተ መንግሥት አጸድ ሥር ተመርምሮ ያልተደረሰባቸው ድንቅ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ በአብያተ መንግሥታቱ አጸደ ሥር ገና ያልተገለጡ ብዙ ምስጢራዊ ጉዳዮች አሉ ይላል ፋንታሁን፡፡ የከበሩ ውድ ምንጣፎች፣ የሀር መጋረጃዎች፣ የወርቅ ጽዋዎች፣ በወርቅ የተለበጡ ጌጣጌጦች፣ በአልማዝ ያጌጡ የነገሥታቱ መገልገያ እቃዎች፣ እስካሁን ያልተዳደሰሱ ምስጢራዊ ሥፍራዎች፣ እጅግ የተዋቡ የነገሥታቱ አልባሳት በዚያ ያመረ ቤተ መንግሥት ውስጥ ኖረዋል፡፡

ጎንደር በረቀቁ ቅርሶች የተዋበች፣ ውብና ድንቅ ከተማ ናት፡፡ ቤተ መንግሥቱን በግምጃ ቤት ማርያም ዙሬ፣ በአደባባይ ኢየሱስ ደርሼ፣ በቆብ አስጥል ሾልኬ፣ እልፍኝ ጊዮርጊስን፣ አጣጣሚ ሚካኤልን አይቼ ዞርኩት ታይተው የማይጠገቡ እልፍ ጥበቦችን ተመለከትኩ፡፡ አሥራ ሁለቱን በሮች እየቆጠርኩ፣ በቤተ መንግሥቱ አጸድ ሥር እየተመላለስኩ ቃኘሁት፡፡ ውበቱን መግለጽ እንደምን ይቻላል? ግርማውን መንገር እንዴት ይኾናል? አብያተ መንግሥታቱን ባየሁ ቁጥር እገረማለሁ፣ እደነቃለሁ፣ የአባቶችን ጥበብ አስባለሁ፡፡ እኔ ብቻ አይደለሁም ለአሥር ዓመታት በዚያ በተዋበ ቤተ መንግሥት እየተመላለሰ ያስጎበኘው፣ ታሪክ የነገረው ፋንታሁንም በየቀኑ የረቀቀ ነገር ይታየኛል ይላል፡፡ በረቀቀ ጥበብ የተሠሩትን ቅርሶች መመርመር እሻለሁ፣ የሕንጻው ምስጢር ከብዙ ነገር የተሻገረ ነው ይላል ፋንታሁን፡፡ ጎንደር በዙሪያ ገባዋ የረቀቁ ነገሮችን የታቀፈች ናት፡፡ ከአብያተ መንግሥቱ ወጣ ሲሉም ታይተው የማይጠገቡ ታሪካዊና መንፈሳዊ ሥፍራዎች ሞልተዋል፡፡

እነኾ ጥምቀት ቀርቧል፡፡ ዓይኖች ሁሉ ወደ ጎንደር አነጣጥረዋል፣ ልቦች ሁሉ ወደ ጎንደር ለመሄድ አስበዋል፡፡ እግሮች ሁሉ ወደ ጎንደር ጉዞ ጀምረዋል፡፡ ሙሽራዋ ጎንደር እንግዶቿ የሚያርፉበትን እልፍኙን አሳምረዋለች፣ ሰፊውን አዳራሽ አስውበዋለች፡፡ እንግዳ መቀበል የምታውቀው፣ ስሞት አፈር ስኾን እያለች የምታቀማጥለው ጎንደር፣ ጠጅ፣ እየጣለች፣ ጠላ እየጠመቀች፣ ጮማ እየቆረጠጭ፣ ወይን እየቀዳች በአባትና እናት ወግና ባሕል እንግዶቿን ኑ ከታሪኬ ላሳያችሁ፣ ከፍቅሬ ላካፍላችሁ እያለች ነው፡፡

“የጎንደር እልፍኝ አቤት ስፋቱ
የተመቸ ነው ቤተ መንግሥቱʺ እንዳለች ከያኟ የጎንደር እልፍኝ ሰፊ ነው፣ ቤተ መንግሥቱም የተመቼና ያማረ ነው፡፡ የሚሄደውን ሁሉ በፍቅርና በክብር ይቀበላል፡፡

ሂዱ ጎንደር እልፍኙን አሳምራ፣ ቤተ መንግሥቱን አስውባ እየጠበቀች ነው፡፡ ታሪክ የከበባትን፣ እምነት የጸናባትን፣ ሀገርና ሠንደቅ የሚከበርባትን ታላቅ ከተማ ይመልከቱ፡፡ ያን ጊዜ የሠንደቅን ክብር፣ የሀገርን ፍቅር ያያሉ፡፡ የተከበረውን ሃይማኖታዊ ሥርዓት አይተው ይደነቃሉ፡፡ ጥምቀትን እልፍኙን ባሳመረችው፣ ቤተ መንግሥቱን ባስዋበችው ተሞሽራ በኖረችው ጎንደር ያሳልፉ፡፡ ጎንደር በጥምቀት ትደምቃለች፣ በጥምቀት ከፍ ከፍ ትላለች፡፡ በጥምቀት ትሞሸራለች፣ በጥምቀት በልዩ ግርማ ትነግሳለች፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዓለም ከተማ ነዋሪዎች ላይ ቅሬታ የፈጠረው የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት
Next articleየሀገር ባለውለታ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት/ንጉሰ ጎጃም ወከፋ/ !