በዓለም ከተማ ነዋሪዎች ላይ ቅሬታ የፈጠረው የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት

166

ባሕር ዳር: ጥር 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከሦስት ዓመታት በፊት ግንባታው የተጀመረው የኮከብ መስክ ዓለም ከተማ አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት በነዋሪዎች ላይ ቅሬታ ፈጥሯል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ የእንሳሮን እና የመርሐቤቴን ወረዳዎች የሚያገናኝ ነው። ፕሮጀክቱ መስከረም 2015 ዓ.ም መጠናቀቂያ ጊዜው ቢኾንም አሁን ድረስ የፕሮጀክቱን ግማሽ እንኳን መፈጸም አልተቻለም።

የመንገድ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጫና ማሳደሩን ያነጋገርናቸው የመርሐቤቴ ወረዳ ዓለም ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ካነጋገርናቸው ውስጥ አቶ ተፈራ ከተማ እንዳሉት ከሦስት ዓመት በፊት የኮንክሪት አስፋልት ሥራ ቢጀመርም ግንባታው በመጓተቱ ምክንያት ማኅብረተሰቡ ለእንግልት ፤ተሽከርካሪዎች ደግሞ ለከፍተኛ ጉዳት እየተጋለጠ ነው።

ከዓለም ከተማ ደብረብርሃን 94 ብር የነበረው የትራንስፖርት ክፍያ 200 ብር ድረስ እየተከፈለ ነው። ከዓለም ከተማ አዲስ አበባ 180 ብር የነበረው ክፍያ ደግሞ 400 ብር እንዲከፍሉ መገደዳቸውን ነው የነገሩን።

የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪው በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ብቻ ሳይኾን በጭነት ተሽከርካሪዎችም ጭምር የሚፈፀም ነዉ። ለዚህም ከአዲስ አበባ በሚመጡ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ በመፈጠሩ ኅብረተሰቡ ገዝቶ ለመጠቀም እየተቸገረ መኾኑን ተናግረዋል። አካባቢው ከፍተኛ የተፈጥሮ ሃብት ቢኖረውም መንገዱ ባለመልማቱ ባለሃብቶች ወደ አካባቢው ገብተው እንዳያለሙ እንቅፋት ፈጥሯል።

የሕዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪ አቶ ዝምበላቸው ቦጋለ እንደገለጹት የዓለም ከተማ ኮከብ መስክ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ሥራ በተቀመጠለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ተሽከርካሪዎች ለከፍተኛ ጉዳት እና ብልሽት እየተጋለጡ ነው። በየጊዜው በመንገዱ ላይ በሚደርሰው ጉዳት አሽከርካሪዎች አገልግሎት ለመስጠት ፍላጎት እንደሌላቸው አስረድተዋል። መንገዱ በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ አገልግሎት እንዲሰጥ መንግሥት ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የደብረ ብርሃን እና አካባቢው ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ ኢንጂነር ንጋቱ ውድነህ እንደተናገሩት ከኮከብ መስክ ዓለምከተማ የአስፋልት የመንገድ ግንባታ በሦስት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ቢታሰብም በአሁኑ ወቅት አፈፃፀሙ ከ37 ከመቶ አይበልጥም። ሥራዎችን በተቀመጠው ጊዜ ያለማስፋፋት፣ የግንባታ ቁሳቁሶችን በወቅቱና በበቂ ሁኔታ ከውጭ አለማስገባት፣ የገንዘብ ፍሰቱ ደካማ መኾን፣ አስፈላጊውን የሰው ኀይል እና ማሽነሪ ወደ ሥራው አለማሰማራት በተቋራጩ የታዩ ችግሮች ናቸው ብለዋል።

አስፈፃሚው ተቋም ክፍያን በወቅቱ አለመክፈል፣ ለአርሶ አደሩ የካሳ ክፍያ በጊዜ ከፍሎ ቦታን ነፃ አድርጎ አለማስረከብ ተቋራጩ በተፈለገው ፍጥነት ሥራውን እንዳይከውን አድርጎታል።

ከዚኽም ባሻገር በዓለም አቀፉ ደረጃ የተፈጠረው የኮቪድ ወረርሽኝ እና በጦርነቱ ምክንያት ሥራው መቋረጡ፣ የፕሮጀክቱ የዲዛይን ክለሳ ና በተወሰኑ አካባቢዎች የመሬት መንሸራተት ምክንያት የማራዘሚያ ጥያቄ መቅረብ ሌላኛው ለመዘግየቱ በምክንያትነት ተቀምጠዋል። አኹን ላይ በአስፈፃሚው እና ተቋራጩ በኩል የነበሩ ችግሮች በመፈታታቸው መስከረም 2016 ዓም የመንገዱን ግንባታ ተጠናቅቆ ክፍት እንደሚኾን ኢንጂነር ንጋቱ ተናግረዋል።

👉የኮከብ መስክ ዓለም ከተማ የመንገድ ፕሮጀክት ከሙከጡሪ – ዓለም ከተማ – ጋሸና የሚደርሰው የመንገድ ፕሮጀክት አካል ነው።
👉መንገዱ ከሙከጡሪ ኮከብ መስክና ከኮከብ መስክ ዓለምከተማ በሁለት ተከፍሎ እየተከናወነ የሚገኝ ነው።
👉መንገዱ የሚገነባው በቻይናው ሰቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ነው።
👉መንገዱ 47 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ይረዝማል።
👉ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለታል።
👉የመንገዱ ኮንትራት የተፈረመው ግንቦት 2011 ዓ.ም ሲኾን ሥራው የተጀመረው መስከረም 2012 ዓም ነበር።
👉በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ማለትም መስከረም 2015 ዓ.ም የመጠናቀቂያ ጊዜ ተይዞለት ነበር።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ የጋራ ልዩ ስብሰባ ዛሬ ይካሔዳል፡፡
Next articleʺሙሽራዋ ተሞሽራለች፣ እልፍኙንም አስውበዋለች”