
ባሕር ዳር: ጥር 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በፌዴራል መንግሥት እና በህወሓት አመራሮች መካከል በደቡብ አፍሪካ እና በኬኒያ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ በትናንትናው ዕለት የመጀመሪያ ዙር ከባድ መሳሪያ ርክክብ ተደርጓል።
ርክክቡ ከመቐለ ከተማ 36 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አጉላ ካምፕ የተከናወነ ሲሆን፤ በርክክቡ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ ታዛቢዎችም ተገኝተዋል።
በቀጠናው የተሰማራው ሠራዊት አመራር ሌተናል ኮሎኔል አለሜ ታደለ በመንግሥታችንና በህወሓት አመራሮች መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት የተለያዩ ዓይነት ከባድ መሳሪያዎችን መረከባቸውን ገልፀዋል።
ህወሓት ለመከላከያ ሠራዊታችን ያስረከባቸው የመሳሪያ ዓይነቶችም ብረት ለበስ ታንኮች፣ የተለያዩ ሚሊ ሜትር መድፎች፣ ሮኬቶች፣ ዙዎች፣ ሞርታሮች እና ፐምፐን ያጠቃለለ መኾኑን ሌተናል ኮሎኔል አለሜ ታደለ ተናግረዋል።
የርክክብ ሥነ-ሥርዓቱን ለመታዘብ የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ አረካካቢ ኮሚቴዎች ተገኝተዋል። ከአረካካቢዎች መካከል ብርጋዴር ጄነራል አድዋ ልቡካን ፒተር በሁለቱም ወገኖች በኩል እየተደረገ ያለው የከባድ መሳሪያ ርክክብ የተጀመረውን የሰላም ጉዞ የሚያጠናክር መኾኑን ነው የገለጹት።
በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥትና በህወሓት መካከል የተደረሰው ሰላምን የማስፈን ተግባር ዓለምን የሚስደንቅ መኾኑን ጠቅሰው ለመላው ሕዝብና ስምምነቱን ተግባራዊ እያደረጉ ላሉ አካላት ምስጋና ማቅረባቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!