
‹‹ደም ለግሰን በደም መፍሰስ ሕይወታቸውን የሚያጡ ወገኖቻችን መታደግ ትልቅ የሰብዓዊነት ጥግ ነው፡፡›› ለ86ኛ ጊዜ ደም የሚለግሱት ግለሰብ
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 15/2012 ዓ.ም (አብመድ) ነዋሪነታቸው በደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ነው፡፡ የሚተዳደሩት ደግሞ በግል ሥራ ነው፡፡ ከ26 ዓመት በፊት ነበር ደም መለገስ የጀመሩት፡፡ አሁን ላይ ደግሞ በኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ደም ለጋሾች ማኅበር መሥራች እና የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ናቸው፤ አቶ ሙሉጌታ ይርጋ፡፡
አቶ ሙሉጌታ ደም መለገስ የጀመሩት በ1985 ዓ.ም ነው፤ ዛሬ እየተካሄደ በሚገኘው ሀገር አቀፍ የደም ልገሳ ቀንም ለ86ኛ ጊዜ ደም እንደሚለግሱ ነግረውናል፡፡ አቶ ሙሉጌታ ደም ለመለገስ መነሻ የሆናቸው አንድ ግለሰብ በክረምት ወራት የውኃ ማፋሰሻ ቱቦ ውስጥ ወድቆ ጉዳት ደርሶበት በማየታቸውና ግለሰቡን ለመታደግ ከቤታቸው ደርሰው ሲመለሱ ሕይወቱ አልፎ ማግኘታቸው ነው፡፡ የግለሰቡን ሕይወት ማትረፍ ባለመቻላቸውም ‹‹በራሴ እጅ እንደጠፋች አድርጌ ነው የማየው›› ብለዋል በፀፀት ስለሁኔታው ሲናገሩ፡፡
በወቅቱ ደሴ ላይ ቀይ መስቀል ስለነበር በራሳቸው ተነሳሽነት ከኮምቦልቻ ደሴ 23 ኪሎ ሜትር በመመላለስ ደም መለገስ እንጀመሩ ነው አቶ ሙሉጌታ የተናገሩት፡፡ ደም በመለገሳቸውም የደረሰባቸው ችግር እንደሌለ አመልክተዋል፡፡ ‹‹በሚሊዮን የሚቆጠሩ የደም ሕዋሳት ይሞታሉ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ይተካሉ፡፡ የደም ሕዋሳት ያለምንም ጥቅም ከሚሞቱ ደም ለግሰን በደም መፍሰስ ሕይወታቸውን የሚያጡ ወገኖቻችን መታደግ ትልቅ የሰብዓዊነት ጥግ ነው›› ብለዋል አቶ ሙሉጌታ፡፡
በተከታታይ ደም በመለገስ በክልሉም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚወዳደራቸው አልተገኘም፡፡ ደም ሲለግሱ ከቤተሰቦቻቸው ተቃውሞ ይደርስባቸው እንደነበርም ነው አቶ ሙሉጌታ ለአብመድ የገለጹት፡፡ ይሁን እንጅ ደም መለገስ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያስከትልና ይልቁንም ለጤና ጠቀሜታ እንዳለው በሂደት በመረዳታቸው አንደኛዋ እህታቸው ለ11ኛ ጊዜ ደም የለገሰች መሆኑንና ሌሎች ቤተሰቦቻቸውም እየለገሱ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
‹‹የምለግሰው ደም ነው፤ እንደ ደም ሲለገስ ጉዳት የማያስከትልና የሌላውን ሕይወት መታደግ የሚችል ከደም በላይ ሌላ ስጦታ ቢኖርም መለገስ እችል ነበር›› ብለዋል አቶ ሙሉጌታ፡፡
አቶ ሙሉጌታ ደም ከመለገስ ባለፈ በ2007 ዓ.ም ከክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ፈቃድ ወስደው የኮምቦልቻ ደም ለጋሾች ማኅበርን መስርተዋል፡፡ ማኅበሩ አሁን ላይ 530 የደም ለጋሽ አባላት እንዳሉት አስታውቀዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ማኅበሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተመሥርቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ፎቶ፡- ከፋይል