
ባሕር ዳር: ጥር 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በግጭቶች የወደሙ ጤና ተቋማትን መልሶ ከማደራጀትና ወደ ስራ ከመመለስ እንደዚሁም ለዜጎች የጤና አገልግሎት ከማድረስ አኳያ የተሰሩ ስራዎችን አስመልክቶ የጤና ሚኒስቴር ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ ሰጥቷል፡፡
መግለጫውን የሰጡት ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ.ር) ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው በነበሩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ምክንያት ህዝብ የሚገለገልባቸው የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፤ የህክምና ግብዓት ማከማቻ ተቋማት እና ሌሎችም መውደማቸውን አንስተዋል። በቀጠናው ላሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የጤና አገልግሎቶችን በተደራጀ ሁኔታ አገልግሎት ለመስጠት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል ብለዋል፡፡
ችግሩን ለመቅረፍም የጤና ሚኒስቴር ከተለያዩ ተቋማት እና ከአለም ዓቀፍ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለጤና አገልግሎት አስላፈጊ የሆኑ ድጋፎችን በተለያዩ ክልሎች የማድረስ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡
የሰብዓዊ ርዳታ፣ የሕይዎት አድን ህክምና ፣ የስርዓተ ምግብ እንዲሁም የጤና አገልግሎትን ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። የጤና አገልግሎቶችን መልሶ የማቋቋም ሥራም እየተከናወነ ይገኛል። ከጤና ሚንስቴርና ከተጠሪ ተቋማት የተውጣጡ ከ30 በላይ ቡድን በአላማጣ፤ ኮረም፤ሽሬ፤ አክሱምና አድዋ ላይ በሁለት ዙር ተሠማርተው ከሰላም ስምምነቱ ጀምሮ ሥራዎችን እያገዙ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ በአላማጣና ሽሬ ኮሪደር ላይ ወደ ሥራ በተመለሱ 12 ሆስፒታሎችና 28 ጤና ጣቢያዎች ከ95% በላይ ሠራተኞች ወደ ሥራ ተመልሰዋል ተብሏል፡፡
በአጠቃላይ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ አስፈላጊ የሆኑ መድሃኒትና ሌሎች ግብዓቶች በመንግሥት ማድረስ መቻሉ ተነስቷል፡፡
እንደ ሀገር በተለያዩ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ለወደሙ የጤና ተቋማት የመልሶ ግንባታ ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገልጠዋል፡፡
እንዳልካቸው አባቡ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!