
ጎንደር: ጥር 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከአምስት ወረዳዎችና ከአይከል ከተማ አስተዳደር የተወጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች በጭልጋ ወረዳ ሕዝባዊ የሰላም ውይይትና የምሥጋና መርሐ ግብር አካሂደዋል።
አሁን ለመጣው ሰላም ከፊት ኾነው ላገለገሉት የአማራ ልዩ ኃይል ፣ ለአካባቢው የፀጥታ ኀይሎች ፣ለሀገር ሽማግሌዎችና ለሃይማኖት አባቶች ማኅበረሰቡ ምስጋና አቅርቧል። ወረዳው ሰላሙ እየተረጋገጠ መኾኑን የጠቀሱት ነዋሪዎቹ ወደ ልማት መግባታቸውንም ጠቅሰዋል።
የጭልጋ ወረዳ አሥተዳዳሪ አዛናው አደባ መንግሥት ከማኅበረሰቡና ከማዕከላዊ ጎንደር አማካሪ ምክር ቤት ጋር በመተባበር በሠራው ሥራ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱንም ተናግረዋል።
አስተዳዳሪው ሰላሙን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ማኅበረሰቡ ወደ ልማት ፊቱን ማዞሩን ነው ያስገነዘቡት። የሕዝቡ የልማት ጥያቄዎችም መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር አማካሪ ምክር ቤት ሰብሳቢ ድርጅት አድማሱ የአካባቢዉን ሰላም ለማጠናከር በጫካ የነበሩትን የማስገባትና ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል። እስካሁንም 300 ታጥቀው የነበሩና በሰላም እጃቸውን የሠጡ ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለዋል ብለዋል።
በቀጣይም ያልገቡትን የመመለስና ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል። አቶ ድርጅት እንዳሉት የዛሬው የሰላም ውይይትና የምሥጋና መርሃ ግብር አንድነትን ለማጠናከርና ግልጽነትን ለመፍጠር አግዟል። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና ውይይቱም ይቀጥላል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- አገኘሁ አበባው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!