የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በትብብር ለመሥራት ተስማሙ።

131

አዲስ አበባ: ጥር 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በትብብር ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

ሥምምነቱን የተፈራረሙት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሬሽን ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ሰጠኝ አቡሃይ እና የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ናቸው። ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በቀጣይ በበርካታ ዘርፎች ላይ በትብብር ለመሥራት የሚያስችላቸው እንደኾነ ተገልጿል፡፡

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ሰጠኝ አቡሃይ በሥምምነቱ አሚኮ የከተሞች ሁለንተናዊ እድገት እንዲፋጠን የሚያስችሉ የሚዲያ ሥራዎችን በመሥራት ሰፊ ልምድ አለው ብለዋል፡፡ በ10 ቋንቋዎች ኅብረተሰቡን በስፋት ተደራሽ የሚያደርጉ ሥራዎችን እያከናወነ ስለመኾኑም ተናግረዋል፡፡

አሚኮ የአብሮነት ትስስርን ለመፍጠር ልዩ ፕሮግራም ቀርጾ በሁሉም ክልሎች እየሠራ እንደኾነ ያስረዱት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ሁለንተናዊ የልማት ሥራው ወደ ኅብረተሰቡ እንዲደርስ ለማስቻል ስምምነቱ እንደሚያግዝ ነው ያስገነዘቡት። ከከተማና መሠረተ ልማት ጋር የተያያዙ ሥራዎችንም ከሕዝቡ የመልማት ፍላጎት ጋር አስተሳስሮ ወደ ሕዝቡ ለማድረስ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በጽኑ እንደሚተጋ ነው የገለጹት፡፡

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው በከተሞች እያደገ የመጣውን የመልማት ፍላጎት ውጤታማ ለማድረግ፤ የዜጎችን የቤት ፍላጎት በእውቀት በመምራት በዘላቂነትና በውጤታማነት ለመፍታት፤ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ የኾኑትን የተቋሙ ሥራዎች ሕዝቡ እንዲያውቅ ለማድረግ ከአሚኮ ጋር በትብብር መሥራት አስፈላጊ ኾኖ አግኝተነዋል ብለዋል።

ከተሞችን ምቹና ጽዱ ለማድረግ እንዲሁም በመሰረተ ልማት ዘርፉ ላይ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ለሕዝቡ ለማሳወቅ ያግዛል። ከኅብረተሰቡ ጋር ያለውን ቅሬታ ለመሥማት እና ተቋሙ ከኅብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን ጉዳዮች ለማሳወቅ ሥምምነቱ እንደሚያግዝም ነው ሚኒስትሯ በአፅንኦት የገለጹት።

በቀጣይም ሌሎች የልማት ሥራዎችን ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በቅንጅት እና በትብብር ለመሥራት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ዝግጁ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታደለ ፋንታሁን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአቶ ደመቀ መኮንን ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ።
Next articleየአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በትብብር ለመሥራት ተስማሙ።