
ቱሪዝሙን ከሥራ ዕድል ጋር የሚያስተሳስር የስዕል እና የእደ ጥበብ ፌስቲቫል በላልይበላ ከተማ ተጀምሯል።
በአይነቱ አዲስ የሆነ የስዕል እና የእደ ጥበብ ፌስቲቫል በላልይበላ ከተማ ዛሬ ጥቅምት 15/2012 ዓ.ም እየተካሄደ ነው፡፡
አረንጓዴ የማምረቻ ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ፕሮጀክት፣ የንግድና ዘርፉ ማኅበራት ምክር ቤት እና የላልይበላ ከተማ አስተዳድር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት በጋራ ባዘጋጁት የመጀመሪያው ‹‹ላልይበላ የስዕል እና የእደ ጥበብ ፌስቲቫል›› ላይ 30 ተሳታፊዎች ምርቶቻቸውን አቅርበዋል፡፡
የአካባቢውን የባህል፣ የእምነት እና የእሴት መገለጫ ውጤቶች በተለያዩ የጥበብ ሥራዎች አዘጋጅተው ያቀረቡት ተሳታፊዎቹ በአረንጓዴ የማምረቻ ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ፕሮጀክት የቴክኒክ እና በአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል ተብሏል፡፡
ከሮሃ እስከ ላስታ፣ ከይምርሀነ ክርስቶስ እስከ ናኩተ ለአብ፣ ክብልብላ ጊዮርጊስ እስከ አሸተን ማርያም፣ ከላልይበላ ወቅር አብያተ ክርስቲያናት እስከ ነገስታት መካነ መቃብር እና ሌሎች ጥንታዊ የታሪክ አሻራዎችን አቅፎ የያዘውን የላልይበላ እና አካባቢው የመስህብ ሀብት በየዓመቱ ቁጥሩ የበዛ የውጪ ሀገራት እና የሀገር ውስጥ ጎብኝ ያየዋል፡፡
ነገር ግን ቱሪዝሙን ከሥራ ዕድል ፈጠራ እና ከአካባቢው ፀጋዎች ጋር አስተሳስሮ መሥራት ባለመቻሉ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በተለይም ወጣቱን ተጠቃሚ ማድረግ ላይ ውስንነቶች ይስተዋላሉ።
ወጣቶቹ እና ሌላው ማኅበረሰብ የአካባቢውን ፀጋዎች በመጠቀም እና እሴት በመጨመር ከቱሪዝም ፍሰቱ ጋር እንዲተሳሰር በማሰብ ነበር አረንጓዴ የማምረቻ ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ፕሮጀክት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ወደ ሥራ የገባው፡፡ በዚህም ከ30 በላይ ወጣቶችን አደራጅቶ በእደ ጥበቡ ዘርፍ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየሰራ ነው። የወጣቶቹ ሥራ የቀረበበት የስዕል እና የእደ ጥበብ ፌስቲቫልም በሀገር ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ይገኛል፤ ለሁለት ቀናትም ይቆያል፡፡
በፌስቲቫሉ መልዕክት ያስተላለፉት የከተማ አስተዳድሩ ከንቲባ ሙሉጌታ ወልደ ሚካኤል ‹‹ከተማ አስተዳደሩ ቱሪዝሙን ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር አስተሳስሮ ለመሥራት የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀመ ነው›› ብለዋል፡፡
ያነጋገርናቸው ተሳታፊዎችም ይህን መሰል የእድ ጥበብ ፌስቲቫል በከተማዋ እና በሌሎች ቦታዎች ቢዘጋጅ ለገበያ ትስስር እና ለባህል ለውውጥ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
የሽመና፣ የቆዳ፣ የሸክላ፣ የከበሩ ድንጋዮች ጌጣጌጥ፣ ስዕል እና ቅርፃ ቅርፅ በፌስቲቫሉ ለአውደ ርዕይ ቀርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከላል ይበላ