
ባሕርዳር: ጥር 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አዲሱን የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግን በጽሕፈት ቤታቸውን ተቀብለው አነጋግረዋል።
ውይይቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት የበለጠ በሚጠናከርበት ሁኔታ እና በሌሎች ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ውይይቱን በተመለከተ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት፣ “የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት አሁንም ጸንቶ ቀጥሏል። የዛሬው ውይይታችን ይህንን እና በልማት የምንጋራውን ስልታዊ የጋራ ዓላማ፤ እንዲሁም አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን አጉልቶ አሳይቷል” ብለዋል።
የመጀመሪያውን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በአፍሪካ እያደረጉ ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቀዳሚ መዳረሻቸውን ኢትዮጵያ አድርገዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በአፍሪካ ጉብኝታቸው ጋናን ቤኒን አንጎላ እና ግብፅንም የሚጎበኙ ይሆናል።
በኢትዮጵያም እያደረጉ ያሉት ጉብኝት የሀገራቱን ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
