በጦርነቱ የስነልቦና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ሊያግዙ የሚችሉ ፕሮጀክቶች ይፋ ኾኑ።

117

ባሕር ዳር: ጥር 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በጦርነቱ ምክንያት የበርካታ ወገኖች ሕይወት አልፏል፤ ንብረትም ወድሟል፤ በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የስነልቦና ጉዳትም ደርሷል። ይህን ጉዳት ለመቅረፍ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ።

የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮም በአዲስ ሕይወት ሪሃብሊቴሽን ኤንድ ሪኢንቴግሬሽን አሶሲዬሽን ግብረሰናይ ድርጅት አስተባባሪነት ከ11 መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ጋር በሰላም ግንባታና በግጭት አፈታት ዙሪያ በባሕር ዳር ምክክር አካሂዷል።

በምክክሩም ደርጅቶቹ በሚያካሂዱት የፕሮጀክት ሥራ በጦርነቱ የተጎዱትን ወገኖች መልሶ የማቋቋምና ማረጋጋት እንዲኹም ተመሳሳይ ጉዳቶች እንዳይከሰቱ ኅብረተሰቡ ምን ማድረግ እንዳለበት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንደሚሠሩም ነው የተገለጸው።

የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ምክትል ኀላፊ መሰረት አዱኛ ፕሮጀክቶቹ በጦርነቱ ምክንያት የተጎዳው ማኅበረሰብ ከጉዳቱ አገግሞ ለሰላም ዘብ እንዲቆም እንደሚሠራም ነው ያስረዱት።

የአዲስ ሕይወት ሪሃብሊቴሽን ኤንድ ሪኢንተግሬሽን አሶሲዬሽን ዋና ዳይሬክተር አብዱራህማን ከማል በጦርነቱ ምክንያት ስነልቦናው ለተጎዳ ማኅበረሰብ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ የፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓላማ ሕዝቡ ከስነልቦና ጉዳቱ ወጥቶ ሰላም እንዲሰፍን ማስቻል ነውም ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ድጋፍ ፕሮግራም፣ የፕሮግራም መሪ ሰላማዊት መንክር በኢትዮጵያ የተለያየ ጉዳት በደረሰባቸው ስድስት ክልሎች ላይ አተኩረው እየሠሩ እንደኾነ ጠቁመዋል። በአማራ ክልል ለመሥራት የተስማሙ ድርጅቶችም በክልሉ በስድስት ዞኖችና 26 ወረዳዎች ላይ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል። ፕሮጀክቶቹ ለአምስት ወራት እንደሚቆዩ ያስረዱት ወይዘሮ ሰላማዊት በአጠቃላይ 26 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ፕሮግራም አስተባባሪዋ ድርጅቶቹ የስነልቦና ድጋፍ እና የሙያ ድጋፍ ስልጠና እንደሚሰጡም ተናግረዋል። በኅብረተሰቡ ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ በመኾኑ መንግሥት፣ ግብረሰናይ ድርጅቶችም ኾነ ሌሎች ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ የድርጅቱ ትኩረት እንደኾነም ነው ያስረዱት።

በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ ባለሙያ ሌሊሳ ጣሰው፤ ሚንስትር መሥሪያ ቤቱ በሰላም ግንባታ ዙሪያ ስለሚሠራ የተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲደገፉ የማመቻቸት ተግባርን ይፈጽማል ብለዋል። ሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ ለተጎዱ አካባቢዎች ድጋፍ እንዲደርስ የማመቻቸትና የመከታተል ሥራን እንደሚሠራም ባለሙያው አስረድተዋል።

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኢትዮጵያ ልማትና የገጽታ ግንባታ ሥራ ላይ የላቀ ተሳትፎ ላደረጉ ዳያስፖራዎች እውቅና ሊሰጥ ነው።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ።