
ባሕርዳር: ጥር 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማትና የገጽታ ግንባታ ሥራ ላይ የላቀ ተሳትፎ ላደረጉ ዳያስፖራዎች የእውቅና መርሐግብር ሊካሄድ መኾኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ።
የእውቅና መርሐግብሩን በማስመልከት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በኢትዮጵያ የልማት እንቅስቃሴ እንዲሁም የገፅታ ግንባታ ሥራ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ የዳያስፖራ አባላት ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም የእውቅና መርሐ ግብር ይካሄዳል ብለዋል።
በገንዘብ እና በእውቀት ጭምር ለአገራቸውና ሕዝባቸው የላቀ ተሳትፎ በማድረግ የሚጠቀሱ ዳያስፖራዎችም እውቅና ይሰጣቸዋል ብለዋል።
በመኾኑም ከ25 የተለያዩ የዓለም አገራት የተውጣጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች እውቅና የሚሰጣቸው መኾኑን ጠቁመዋል።
በእውቅና መርሐ ግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ ዳያስፖራዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ኢዜአ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!