
ባሕር ዳር: ጥር 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ናሽናል ጂኦግራፊ መጎብኘት አለባቸው ካላቸው የዓለማችን አምሥት ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል ኢትዮጵያን አካቷል፡፡
ናሽናል ጂኦግራፊ – ብሪታኒያ የፈረንጆቹን 2023 ዐዲስ ዓመት ዕትምን ይዞ ወጥቷል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ አፋር ውስጥ ዳሎልን አካሎ የሚገኘው የደናክል አካባቢ በቀዳሚነት የቱሪስቶችን ቀልብ ይገዛል ተብሎ በዲጂታል ዕትሙ ተጠቁሟል፡፡
የደናክል አካባቢ የምድራችን ደረቁ ፣ እጅግ ሞቃታማው እና ረባዳማው አካባቢ እንደመሆኑ ፈተና እና ጀብዱ የሚወዱ ቱሪስቶች ሳይጎበኙት እንዳያልፉም በመረጃው አስታውሷል፡፡
አካባቢው በውስጡ ጨዋማ ወንዞችን ፣ ቢጫ ቀለም ያላቸው አሲዳማ እና እንፋሎታማ ምንጮችን እንደ ጅረት የሚፈሱ እሳተ-ገሞራዎችን እንደያዘም ጠቅሷል፡፡
ናሽናል ጂኦግራፊ -ብሪታኒያ በተለይ በጎንደር እና በላሊበላ አካባቢ በኦርቶዶክስ አማኞቸ ዘንድ በደመቀ ሥነ-ሥርዓት የሚከበሩት የጥምቀት እና የገና በዓላት ምርጥ የቱሪስት መስኅቦች መሆናቸውን አንስቷል፡፡
በ17ኛው ክፍለ-ዘመን እንደተገነባ የሚነገርለት የጎንደር ቤተ መንግስ እንዲሁም የላሊበላ ውቅር አቢያተ-ክርስቲያናትም መጎብኘት አለባቸው ብሏል-በመረጃው፡፡
በተጨማሪም በተጠቀሱት አካባቢዎች የሚደረጉት ሃይማኖታዊ ጉዞዎች ምግቦች ፣ መጠጦች እና ባሕላዊ ጭፈራዎች ሌላ የቱሪስቶችን ዕይታ የሚስቡ ትዕይንቶች መሆናቸውንም ዘርዝሯል፡፡

ቱሪስቶች የአስደናቂ መልክዓ-ምድሮች እና የበርካታ ጎሳዎች መገኛ የሆነውን እስከ ኦሞ ሸለቆ የሚዘልቀው ደቡባዊ ክፍል ያለውን አካባቢ እንዲጎበኙም ተጠቁሟል፡፡ የዘገበው ኤፍ ቢ ሲ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!