በዘንድሮው የላሊበላ የልደት በዓል ላይ የተመዘገበው የቱሪስቶች ቁጥር ከፍተኛው መኾኑ ተገለጸ።

158

✍️ ከ1 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች ተገኝተዋል።

ባሕርዳር፡ ጥር 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ታኅሣሥ 29 ቀን 2015 ዓ.ም በተከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ላይ ከ 1 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች መገኘታቸውን የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የቢሮው ቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ዲፓርትመንት አስተባባሪ ማንደፍሮ ታደሰ በቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት በተከበረው የገና በዓል ላይ ከ1 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች ታድመዋል።

በሰሜኑ ጦርነት የተነሳ የልደት በዓልን ባለፉት ሁለት ዓመታት በላሊበላ ከተማ በድምቀት ማክበር እንዳልተቻለ አስታውሰው፤ የዘንድሮውን በዓል ግን በተሳካና በሰላማዊ ሁኔታ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ታጅቦ መካሄዱን አስታውቀዋል።

እንደ አቶ ማንደፍሮ ገለጻ፤ በበዓሉ በተሳተፉ ቱሪስቶች አማካኝነት የአገልግሎት ዘርፉም የተሻለ ገቢ እንደተፈጠረለት ይታመናል። በተለይ ሆቴሎች፣ ምግብና መጠጥ አቅራቢ ድርጅቶች እንዲሁም አስጎብኝዎች በኮቪድና በጦርነቱ ምክንያት ተዳክሞ የነበረው ሥራቸው መነቃቃት ተፈጥሯል ብለዋል።

ወደ ላሊበላ የመጡት ቱሪስቶች ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ናቸዉ ፤ ከበዓሉ አከባበር ባለፈ ጎብኝዎች በከተማዋ የሚገኙ ቅርሶችን ተዘዋውረው እንዲጎበኙ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች በዓለም ቅርስነት በተመዘገበው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ተገኝተው በዓሉን በማክበራቸው የቱሪዝም ዘርፉ ገቢ እንዲያድግ ትልቅ ዕድል ተፈጥሯል ነው ያሉት።

የከተማዋና አካባቢው ሕዝብ እንዲሁም የጸጥታ አካላት ቱሪስቶች ወደ ላሊበላ ገብተው እስኪወጡ ድረስ አስፈጊውን ትብብር በማድረግ የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነው። ሕዝቡም እንግዳ ተቀባይነቱን በድጋሚ ያሳየበት አጋጣሚ ስለነበር በርካታ ቱሪስቶች ተደስተው መመለሳቸውን አቶ ማንደፍሮ አስረድተዋል።

በላሊበላ የልደት በዓል ከተሳተፉ ጎብኝዎች መካከል አንዱ የኾኑት በኢትዮጵያ የቻይና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዛሃኦ ዚዩኣን የልደትን በዓል በላሊበላ ካሳለፉ በኋላ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት በተመዘገበው ላልይበላ በነበረኝ የሁለት ቀናት ቆይታ የኢትዮጵያውያን ወዳጃዊና የሚስብ እንግዳ ተቀባይነት አስደንቆኛል ብለዋል።

በላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ መሠረት በዘንድሮው በዓል ላይ የተመዘገበው የቱሪስቶች ቁጥር ከእስካሁኖቹ የልደት በዓላት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛው ኾኖ ተመዝግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጦርነት ምክንያት ኤሌክትሪክ ሳያገኙ የቆዩ ከተሞች በሁለት ሳምንታት ውስጥ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚኾኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
Next articleኢትዮጵያ መጎብኘት ካለባቸው 5 ምርጥ የዓለማችን የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል አንዷ ነች – ናሽናል ጂኦግራፊ