
ባሕርዳር፡ ጥር 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በጦርነት የተጎዱ እና የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶቻቸው በመውደማቸው ምክንያት ኤሌክትሪክ ሳያገኙ የቆዩ ከተሞች በሁለት ሳምንታት ውስጥ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚኾኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሰሜን ዲስትሪክት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ብዙወርቅ ደምሴ እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ጊዜ በአማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልሎች በጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ከተሞች የመብራት አገልግሎት በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ ነበረበት ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ ነው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተጠቀሱት ክልሎች በዞን እና በወረዳ ደረጃ ጦርነት በተካሄደባቸውና ውድመት በደረሰባቸው አካባቢዎች የሚገኙ 59 ዋና ዋና ከተሞች የተከሰተውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት እጦት ለመፍታት አቅዶ ሲሠራ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ብዙወርቅ፤ ከእነዚህ ከተሞች አብዛኞቹ የመብራት አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ሲቻል ቀሪዎቹ ደግሞ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ያገኛሉ ብለዋል።
ኃላፊው አብነት አንስተው እንዳስረዱትም፤ በትግራይ ክልል ሽራሮ አካባቢ በተጨማሪም አንዳንድ በአማራ ክልል የሚገኙ ከተሞች በተለይም ሳተላይት ከተማ እየተባሉ የሚጠሩ የገጠር ከተሞች በጣም ርቀው የሚገኙ በመሆናቸው በ15 ቀናት ጊዜ ውስጥ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መልሰው ያገኛሉ ብለዋል።
በአፋር ክልል እንደ ኩነማ ያሉ የመብራት አገልግሎት ያጡ ቀሪ ከተሞች ከሦስት እስከ አራት ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
ኃላፊው ጦርነቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ወደነበረበት ለመመለስ ሌብነት፣ የመሠረተ ልማቶች ውድመት፣ የተቀበሩ ፈንጂዎች እና መሰል ችግሮች እንቅፋት ሆነው ቆይተዋል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!