“ለጥበብ የኖረች፣ በጥበብ የነገሠች”

218

ባሕር ዳር: ጥር 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) መልካም ለዛ ታድሏታል፣ ቀና ልብ ተሰጥቷታል፣ ባሕሏን ትወዳለች፣ አጥብቃ ትጠብቃለች፣ ጠብቃ ታስጠብቃለች፣ በየደረሰችበት ሁሉ ኢትዮጵያዊ መልክን፣ ኢትዮጵያዊ ለዛን፣ ኢትዮጵያዊ ወዝን፣ ኢትዮጵያዊ ክብርን፣ ኢትዮጵያዊ ልክን ታስተዋውቃለች፡፡ እርሷ በደረሰችበት ሁሉ ባሕል ይኖራል፣ እርሷ በተገኘችበት ሁሉ ኢትዮጵያዊነት ከፍ ይላል፣ እርሷ በተገኘችበት ሁሉ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ ያሸበርቃል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ከፍ ታደርጋለች፤ በሀገር ፍቅር ተይዛ የሀገር ፍቅር ታስይዛለች፡፡

ብዙዎች እንደ እናት አዩዋት፤ የቀሚሷን ጫፍ ይዘው አጀቧት፤ እርሷን አስቀድመው በመንገዷ ተከተሏት፤ እየተስረቀረቀ የሚወጣው ድምጿ ስንቶችን ከትካዜ አንቅቷል? ሰንቶችን ከባዶነት መልሷል? ብዙዎችን በፍቅር አጣምሯል፣ የተቀያየሙትን አስታርቋል፣ የተከዙትን አፅናንቷል፣ ያዘኑትን ሐዘናቸውን አስረስቷል፡፡

በትዝታ በደስታ አስለቀሰች፣ በአንቺኾዬ አበበች፣ በባቲ አሸበረቀች፣ በአምባሰል ነገሠች፡፡ የቀዬው ሰዎች መረቋት፣ አብዝተው ወደዷት፣ ስሟ የሚጠራ፣ ሥራዋ የሚያኮራ ይኾን ዘንድ ተመኙላት፡፡ በጥበብ ፍቅር በልጅነቷ ተያዘች፣ ፍቅሯን ተከትላ በጥበብ ኖረች፣ በጥበብ ተከበረች፣ በጥበብ ነገሠች፡፡

ማርዬ ይሏታል፣ ማር የኾነች፣ ማር ኾና የኖረች፣ ከልጅነት እስከ ሽምግልና የተወደደች፣ የትናንቱን እና የዛሬውን ትውልድ በድምጿ ገመድነት ያስተሳሰረች፣ በዘመን የሚለያዩ ትውልዶችን በተመሳሳይ ደስታ ያስለቀሰች፣ በደስታ ባሕር ውስጥ ያስዋኘች፣ እርሷ የምተወዳትን ሀገር በጋራ ያስወደደች፣ ስለ ሀገር በጋራ ያዘመረች የጥበብ ንግሥት፡፡

እንኳን ሰው በአዝዋ ገደል ሥር የሚኖሩ አእዋፋት፣ በጦሳ ሸንተረሮች የሚኖሩ የዱር እንስሳት የእርሷን ድምፅ ሲሰሙ ኖረዋል፣ ዝማሬያቸውን አቁመው ቀጠን ብሎ ወደ ሚስረቀረቀው የሴት ድምፅ ጀሯቸውን አዘንብለዋል። ልብን ሰቅዞ የሚይዘውን ጥዑመ ዜማ አድምጠዋል፣ የወሎ ጎበዛዝት እና ወይዛዝርት የእርሷን ድምፅ እየሰሙ የሐረጎ ዳገትን ያለ ድካም ወጥተዋል፣ በአምባሰል ተራራዎች ወጥተው ወርደዋል። እርሷ በምትዘፍንበት አዳራሽ ያለፉ ሁሉ ሳያውቁት ገብተው የድምጿ እሥረኛ ኾነዋል፡፡

የሚያምረው ድምጿን ሹማምንቱ ሰምተውታል፣ ባለችበት መጥተው አድንቀዋታል፣ ወጣቶች፣ ጎልማሳዎች፣ አዛውንቶች አድምጠውታል፣ አድምጠው ተመስጠውበታል፣ አድምጠው ተደስተውበታል፡፡

የሠርግ ወቅት በደረሰ ጊዜ ጠላው ሲጠነሰስ፣ ድግሱ ሲደገስ እኒያ ደጋግ የወሎ ወይዛዝርትና ጎበዛዝት እየተሰባሰቡ ያዜማሉ፡፡ የባሕሉን ጨዋታ ይጫወታሉ፣ ጨዋታው እና ዜማው ሁሉም ባሕሉን ጠብቆ ነው፡፡ ከእነዚህ የወሎ ወይዛዝርት እና ጎበዛዝት መካከል አንዲት ወይዘሮ አለች፤ እርሷ ያልገባችበት ዘፈን አይደምቅም፣ እርሷ ያልገባችበት ሰርግ አይሞቅም፡፡

ከበሮው ሲመታ፣ ማሲንቆው ሲከተል፣ ጭብጨባው ሲደራ ያን ጊዜ እርሷ ትነሳለች፡፡ በሚስረቀረቀው ድምጿ ማዜም ትጀምራለች፡፡ ከዚያ ወዲያማ ማን ችሎ ይቀመጣል፣ ማን ችሎ ዝም ይላል፤ ሰርጉ ይሞቃል፣ ድግሱ ይዋባል፡፡ እርሷ ከውበት ላይ ውበት ጥጨምርበታለች፣ ከፍ ከፍም ታደርገዋለችና፡፡ ሰርጉ ሲጀመር የቀዬው ሰዎች እርሷን ጥሯት ይላሉ፣ እርሷ ተፈልጋ ትጠራለች፣ ስታዜም ውላ ስታዜም ታድራለች፣ ዜማዋ አይሰለችም፣ ለዛዋ አይጠገብም እና ጠላው እየተቀዳ፣ ጠጁ እየወረደ፣ ጮማው እየተቆረጠ ዓለም ይታያል፡፡ እርሷ የበቀለችባት ከድጆ በማሪቱ ትደምቃለች፤ በማሪቱ ታሸበርቃለች፡፡

ማርዬ ወላጅ የመረቃት፣ የቀየው ሰው እየሳመ መልካሙን የተመኘላት፣ አላፊ አግዳሚው እደጊ ተመንደጊ እያላት ያደገች ተወዳጅ ናት፡፡

ከደሴ ከተማ በቅርብ ርቀት የተወለደችው ማርዬ አባቷን እየተከተለች ወደ ደሴ ታቀና ነበር፡፡ ደሴም በመትሄድ ጊዜ በጠጅ ቤት የሚቀርበውን የአዝማሪ ጨዋታ ታስታውል ነበር፡፡ ያን ባየች ጊዜም አስቀድማ ነብሷ ወደ ጥበብ የመራቻት ብላቴና በተወለደችበት ቀዬ የተወደደችበት ለዛ በሌላውም ትወደድበት ዘንድ አሰበች፡፡
አባቷን አብዝታ ትወዳለች፣ እሳቸውም አብዝተው ይወዷታል፣ ማር የኾነች ልጃቸውን ማሪቱ ብለው ስም አውጥተውላት፣ በደስታና በፍቅር ነበር ያሳደጓት፡፡ አባቷ ሲመርቋት ʺ እልፍ አዳሙ ማሪቱ፣ ማሪቱ ይበልሽ” ይሏት ነበር ይባላል፡፡ በመልካም ልብ የተወደደችው ብላቴና ምርቃኗ ደርሶላት እነኾ እልፍ አዳሙ ʺማሪቱ፣ ማሪቱ” ይላታል፤ በየደረሰበት ሁሉ ያነሳታል፡፡ ስለ ልጃቸው ተናግረው የማይጠግቡት አባቷ ይቀኙላትም ነበር፡፡

ʺእረ እናተ ኾዬ ማሪቱ ማርናት
እኔም ብቻ አይደለሁ እናንተም እዩዋት” እያሉ ያወደሷት ያሞግሷታል፤ አባቷ የማሪቱ በጥበብ ዙፋን ላይ የመቀመጥ፣ የጥበብ ካባ የመደረብ፣ የጥበብ ዘውድ የመድፋት ነገር አስቀድሞ ሳይታየቸው አልቀረም ፡፡ አባት የተመኘውን፣ እርሷም ያለመችውን አገኘች፡፡

በተራራ ከብቶች እያገደች፣ እንሥራ ተሸክማ ወንዝ ወርዳ ውኃ እየቀዳች፣ እንጨት ለቀማ ማሰሪያ ጠቅልላ እየወረደች ማሪቱ ታዜማለች፣ በጋራው የሚውሉ እረኞች ድምጿን እየሰሙ ያደንቋታል፣ ዋሽንታቸውን መንፋት ትተው ይሰሟታል፣ ጎበዛዝቱ ጀሯቸውን አዘንብለው በእርሷ ዜማ ይብሰለሰላሉ፡፡ ያቺ በቀዬው በአድባሩ ተወዳጅ የኾነች ልጅ እንደ ቀዬው ጓደኞቿ ሁሉ እልል ተብሎ ተዳረች፤ ያቺ የድግሱ አድማቂ፣ የሰርጉ ባለሟል ጎጆ ቀልሳ፣ ሦስት ጉልቻ ጎልታ ከእናት አባቷ ቤት ወጣች፡፡

ያን የመሰለ ድምጽ ተዳፍኖ ቀረ ተብሎ ነበር፡፡ እርሷ ግን ከተማ ገብታ ከጥበብ ጋር ያላትን ወዳጅነት ማጠናከር ፈለገች፡፡ አደረገችውም፡፡ ማርዬ ደሴ ገባች፡፡ ከዛ በኋላማ የማሪቱ ድምጽ አላፊ አግዳሚውን ሁሉ እየሳበ ያመጣ ጀመር፡፡ የደሴ ጎዳናዎች በማሪቱ ድምጽ ተሞሸሩ፣ ያቺ ድምጸ መልካም ልጅ እየተባለች በየሥፍራው ትጠራ ጀመር፡፡ ከቅኝቶች መፍለቂያ የፈለቀችው ማሪቱ በአራቱ ቅኝቶች እንደ አሻት ማዜም ጀመረች፡፡ መልካም ጉሮሮ የታደለችው ማሪቱ አራቱን ቅኝቶች ከፍ በማድረግም ድርሻዋ ከፍ ያለ ነው፡፡

ማሪቱ በወሎ ላሊበላ የባሕል ቡድን ውስጥ ንግሥት ኾነች፤ በዚያ ታላቅ የባሕል ቡድን ውስጥ ስማቸው ከፍ ብሎ ከሚነሱ የጥበብ ሰዎች እርሷ ከግንባር ቀደሞቹ ተሰለፈች፡፡ ማሪቱን ለመስማት የሚሹ ሁሉ ወደ ወሎ ላሊበላ ያቀኑ ጀመር፡፡ እርሷን ለማዬት የደሴ ነዋሪዎች፣ ደሴን ለመጎብኘትና ለሥራ የሄዱ እንግዶች ብቻ ሳይኾኑ የሀገር መሪዎች ሁሉ ወደዚያ የባሕል ቡድን ይገባሉ፡፡

በአንድ ወቅት ማሪቱ ወደ ምትገኝበት የወሎ ላሊበላ የባሕል ቡድን በቀድሞው የኪነት ቡድን አዳራሽ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ገቡ፡፡ እሳቸውም ቁጭ ብለው ማሪቱን ስትዘፈን ተመለከቱ፡፡ ሌሎችንም በስስትና በደስታ አዩ፡፡ ማሪቱ ያን ጊዜ ስታስታውስ ʺበመጨረሻ ሰብስበው ምን ያስፈልጋችኋል አሉን፣ እኛም መጓጓዣ መኪና የለንም አልናቸው፣ እሳቸውም ለኪነት ቡድኑ አውቶብስ ሰጡ” ትላለች፡፡

በእርሷ ውስጥ ቅኝቶች ጎልብተዋል፣ ባሕል አድጓል፣ የሀገር ፍቅርና አንድነት ዳብሯል፡፡ ታላላቅ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በተሳተፉበት እና የኢትዮጵያን እውነት ለዓለሙ ባሳዩበት የሕዝብ ለሕዝብ ቡድን ውስጥም ነበረች፡፡ በሕዝብ ለሕዝብ በበርካታ የዓለም ሀገራትን ተዘዋውራለች፣ በኢትዮጵያም በተለያዩ ከተሞች እየሄደች ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን ሰብካለች፡፡

የሥርዓት ለውጥ መጥቶ ታላቁ የወሎ ላሊበላ የኪነት ቡድን ችግር ሲገጥመውም ማሪቱ ከጥበቡ አራቀችም፡፡ በሕይወት ጥሪዋ በርትታ ሰራች እንጂ፡፡

ከእርሷ ጋር የነበሩ የጥበብ ሰዎችን እየሰበሰበች ትሠራ ነበር፡፡ ጠርታ ከማትጠግባት፣ አብዝታ ከምትወዳትና ብዙ ነገር ካየችባት ከደሴ ከተማ ርቃ ወደ አዲስ አበባም ሄደች፡፡ በአዲስ አበባም የወሎ ባሕል አምባ ምሽት ቤት ከፍታ መሥራት ጀመረች፡፡ ያቺን ተወዳጅ የባሕል ንግሥት ለማየት የከጀሉ ሁሉ ወደ ቤቷ ያቀኑ ነበር፡፡

የአራቱ ቅኝቶች እመቤት፣ የባሕሏ ንግሥት። አንዱን ታንዱ መደባለቅ አልወድም ትላለች፤ በባሕል ተወለደች፣ በባሕል አደገች፣ በባሕል ታወቀች፣ በባሕል ከፍ ለፍ አለች፣ በባሕል ከበረች፣ በባሕል እንደተከበረች ዛሬም ድረስ አለች፡፡ በበዓላት አይደለም። ሁሉም በባሕል ቀሚስ ታሸበርቃለች፣ ባማረው ሹርባ ትዋባለች፡፡ ʺባሕሌን እወዳለሁ፤ ሰውም የሚወደኝ ባሕሌን ስለምወድ ነው፤ የፈረንጅ ጨርቅ አያስደስተኝም፤ የትም ይሁን የትም ጥበብ ለብሼ ነው የምሄደው፣ ሹርባ እወዳለሁ” ትላለች ማርዬ፡፡

ማርዬ ሁልጊዜ በኢትዮጵያዊ ለዛ፣ በኢትዮጵያዊ ባሕል ትኖራለች፡፡ ከእኔ ቤት ሡሪና ኮት ለሞት መድኃኒት አታገኝምም ትላለች ማርዬ፡፡ ለዛም ነው፡-
“ምስክሬም ይሄው እናት ኢትዮጵያዬ፣
መቼ ወልቆ ያውቃል ሸማሽ ገገላዬʺ ስትል የተቀኘችላት፡፡

ማሪቱ በአንድ ወቅት ለሥራ ወደ አሜሪካ ታቀናለች፡፡ ለአንድ ሳምንት ብቻ ለመቆዬት ነበር አካሄዷ፡፡ ዳሩ ያሰበችው ሳይኾን ቀረና ሳምንታት አልፈው፣ ወራት አልፈው ዓመታት እየተቆጠሩ ማርዬ በሀገረ አሜሪካ ለረጅም ዓመታት ቆዬች፡፡ በሀገረ አሜሪካ እየኖረች በምትወደው ሕዝብና በምትወዳት ሀገሯ ናፍቆት ተቀጣች፡፡ እርሷ ብቻ አይደለችም ኢትዮጵያውያንም በአሻገር እያዩዋት ናፈቋት፣ ያዩዋት ዘንድ ጓጉላት፡፡ ዳሩ በአጭር ጊዜ የሚሰካ አልነበረም፡፡ እንደ ዋዛ 23 ዓመታት ማሪቱ ከምትወዳት ሀገሯ ተለይታ ኖረች፡፡ በዚህ መካከል ልጆቿን እና የቅርብ ዘመዷቿን በሞት ተነጠቀች፡፡ መራር የሐዘን ጊዜያትን አሳለፈች፡፡ በዚያው በሀገረ አሜሪካ እያለች የወሎ ዩኒቨርሲቲ ለወሎ፣ ለኢትዮጵያ በጥቅሉ ኢትዮጵያዊ ለኾነው ጥበብ ላበረከተችው አስተዋፅዖ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷታል፡፡

የማሪቱ ናፍቆት ያንገበገባቸው ተወልዳ ባደገችባት ቀዬ የሚኖሩ ዘመዶቿ ለናፍቆት እንዲህ ሲሉ አዚመውላታል፡፡

ʺቶሎ ነይ ባየሩ በሚገሠግሠው
መቼም በቅሎ አያውቅም እንደ አንቺ ያለ ሰው” ከዛሬ ነገ ትመጣለች እያሉ ለዓመታት በዓይናቸው እየዞረች አልፈዋልና፣ ቶሎ ትመጣ ዘንድ በስንኝ ተመኙ፡፡ እርሷም በአሻገር ኾና የሀገሯ ናፍቆት ሲያንገበግባት በናፍቆት ተቀኝታለች፡፡
ʺሀገሬን ሳስባት ይሸበራል ልቤ፣
ወገን ዘመዶቼን እንደ እህል ተርቤ፡፡
የሰደቱ ዘመን ጊዜው ረዘመና
እንደ ሰው ናፈቀኝ ያገሬ ጎዳና፡፡” በማለት ናፍቆቷን ነግራለች፡፡

ዓመታት አልፈው፣ ዓመታት ተተካክተው ማሪቱ ወደ ሀገሯ ተመልሳለች፡፡ የናፈቃት ሕዝብም አበባ ይዞ ተቀብሏታል፣ ጉልበት እየሳመ አክብሯታል፡፡ እንኳን ደህና መጣሽ፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ
Next articleበጦርነት ምክንያት ኤሌክትሪክ ሳያገኙ የቆዩ ከተሞች በሁለት ሳምንታት ውስጥ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚኾኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።