የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ

144

ባሕር ዳር: ጥር 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አዲሱ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብተዋል።

ቺን ጋንግ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ቺን ጋንግ ለበርካታ ዓመታት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩትን ዋንግ ዩን በመተካት ወደ ስልጣን መምጣታቸው ይታወሳል።

አዲሱ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ በኢትዮጵያ ከሚያደርጉት የመጀመሪያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በተጨማሪ በጋቦን፣ ቤኒን፣ አንጎላ እና ግብፅ ጭምር ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ በተጨማሪም ሚኒስትሩ በአፍሪካ ሕብረት እና በአረብ ሊግ ዋና መስሪያ ቤቶች ተገኝተው ውይይቶችን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሚኒስትሩ ይፋዊ የስራ ጉብኝትም በአፍሪካ እና በቻይና መካከል እየጎለበተ የመጣውን በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ዘርፈ ብዙ ስትራቴጂያዊ አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር ከመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር እንደሚመክሩም ይጠበቃል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዋግ ኽምራ እና ሰሜን ወሎ አካባቢ ለሚገኙ አራት ጤና ጣቢያዎች የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።
Next article“ለጥበብ የኖረች፣ በጥበብ የነገሠች”