በዋግ ኽምራ እና ሰሜን ወሎ አካባቢ ለሚገኙ አራት ጤና ጣቢያዎች የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።

144

ባሕር ዳር: ጥር 1/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ካሊፎርኒያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ሀኪሞች 27 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደርገዋል፡፡

ድጋፉን በሰሜን ካሊፎንያን የሚገኙ የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎችን እና ኢትዮጵያዊያን ኮሚዩኒቲ አባላትን በመወከል የመጡት ዶክተር ቅድስት ኪዳኔ ለጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስረክበዋል።

ዶክተር ቅድስት ኪዳኔ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያዊያን ኮሚዩኒቲ አባላት ቀደም ብለው ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ድጋፉን ማሰባሰብ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

ድጋፉ በዋግ ህምራ እና ሰሜን ወሎ አካባቢ ለሚገኙ አራት ጤና ጣቢያዎች የሚውል መሆኑን ገልፀው÷ በአጠቃላይ 27 ሚሊየን ብር የሚያወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጤና ሚኒስተሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው÷ ድጋፉ ጤና ጣቢያዎችን ሙሉ ለሙሉ አደራጅቶ ወደስራ ለማስገባት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚያደርጉት ድጋፍ መንግስት በጦርነቱ የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ለሚያከናውናቸው ተግባራት አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ዶ/ር ሊያ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት መልሶ ለማቋቋም ለሚከናወኑ ተግባራት እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸው ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ትኩረት በተሰጣቸው የኢንቨስትመንት መስኮች የውጭ ኩባንያዎችን ለመሳብ የሚሲዮኖች ሚና ከፍተኛ ነው” አቶ መላኩ አለበል
Next articleየቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ