“ትኩረት በተሰጣቸው የኢንቨስትመንት መስኮች የውጭ ኩባንያዎችን ለመሳብ የሚሲዮኖች ሚና ከፍተኛ ነው” አቶ መላኩ አለበል

104

ባሕር ዳር: ጥር 1/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ቅድሚያ ትኩረት በተሰጣቸው የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ የሚሳተፉ ተወዳዳሪ የውጭ ኩባንያዎችን ለመሳብ በሚደረገው ጥረት የሚሲዮኖች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።

በአፍሪካ የአመራር ልሕቀት አካዳሚ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች፣ የሚሲዮን መሪዎች እና ተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች የሚሰጠው ሥልጠና እንደቀጠለ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ገለፃ ተሰጥቷል።

ገለፃውን የሰጡት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፥ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከትናንት እስከ ዛሬ ያለውን ገፅታ የዳሰሰ ጽሑፍ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስትሩ ባለፉት አራት ዓመታት ዘረፉን ለማሳደግ የተወሰዱ እርምጃዎችንና የተደረጉ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በተመለከተም ገለፃ አድርገዋል።
በአራቱ ዓመታት ውስጥ ከአሁን በፊት በመንግሥት ቁጥጥር ስር ብቻ ተይዘው የነበሩ ዘርፎች ለግል ኩባንያዎች ክፍት መደረጋቸውን አንስተዋል።

የውጭ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ደረጃ ለመሳብ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን፣ ያጋጠሙ ፈተናዎችና የመፍትሔ አቅጣጫዎችንም አብራርተዋል።

በዚህ ወቅት ሚሲዮኖች በማምረቻው ዘርፍ ብቃት እና አቅም ያላቸው ኩባንያዎችን ወደ አገር ቤት እንዲገቡ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና መጫወት አለባቸው ብለዋል።

ለኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን፣ ያሉ አቅሞችን እና ከመንግሥት የቀረቡ ማበረታቻዎችንም በተገቢው ደረጃ ማድረስ ከሚሲዮኖች ይጠበቃል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በኢትዮጵያ ያለውን ሰፊ የዓሳ ሀብት በቴክኖሎጂ በመደገፍ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብሩን ስኬታማ ለማድረግ ይሠራል” ዶክተር በለጠ ሞላ
Next articleበዋግ ኽምራ እና ሰሜን ወሎ አካባቢ ለሚገኙ አራት ጤና ጣቢያዎች የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።