“በኢትዮጵያ ያለውን ሰፊ የዓሳ ሀብት በቴክኖሎጂ በመደገፍ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብሩን ስኬታማ ለማድረግ ይሠራል” ዶክተር በለጠ ሞላ

127

ባሕር ዳር: ጥር 1/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ ያለውን ሰፊ የዓሳ ሀብት በቴክኖሎጂ በመደገፍ እንደ ሀገር የታቀደውን የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር ስኬታማ ለማድረግ እንደሚሠራ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ገለጹ።

በጋምቤላ ክልል ከ99 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባው ዘመናዊ የዓሳ ማቀነባበሪያና የግብይት ቴክኖሎጂ ማዕከላት ፕሮጀክት ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

በሀገሪቱ ከሚገኙ ወንዞች፣ ሐይቆች፣ ኩሬዎችና ሌሎች የውሃ አካላት በዓመት ከ94 ሺህ 500 ቶን በላይ የዓሳ ምርት ማግኘት እንሚቻል ጥናቶች እንደሚያመክቱ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ያለውን እምቅ የዓሳ ሃብት በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ለተጠቃሚዎች ከማድረስ ብሎም ወደ ኢኮኖሚያዊ ልማት ከመቀየር አኳያ ውስንነቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በዘርፉ የሚታየውን ክፍተት ግምት ውስጥ በማስገባት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በጋምቤላ ክልል ዘመናዊ የዓሳ ማቀናባበሪያና የግብይት ማዕከል መገንባት መቻሉን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በተለይም በቅርቡ በይፋ የተጀመረውን የሌማት ትሩፋት እውን ከማድረግ ባለፈ ከውጪ የሚገባውን የዓሳ ምርት በሀገር ውስጥ በመተካት በኩል የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል።

ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በቀጣይም በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ በማድረግ የዘርፉን ልማት ለማጠናከር እንደሚሠራ ዶክተር በለጠ አስታውቀዋል።

በሚኒስቴሩ የኢኖቬሽንና ምርምር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክትር ባይሳ በዳዳ በኢትዮጵያ ሕዝቡን በበቂ ኹኔታ መመገብ የሚያስችል የዓሳ ሀብት ቢኖርም በዓመት የሚመረተው ከ38 ሺህ ቶን አይበልጥም ብለዋል።

በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ በዓመት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ የዓሳ ምርት ከውጪ እያስገባች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

እንደ ጋምቤላ ክልልም በዓመት ከ12 ሺህ ቶን በላይ የዓሳ ምርት ማግኘት የሚቻል ቢኾንም አሁን ላይ እየተመረተ ያለው 5 ሺህ ቶብ ብቻ መኾኑን ጠቁመዋል።

የተገነባው ዘመናዊ የዓሳ ማቀነባበሪያና የግብይት ማዕከል የክልሉን የዓሳ ሀብት በተሟላ መልኩ ለማልማት የሚስችል መኾኑን ተናግረዋል።

ማዕከሉ የቀዝቃዛ ሰንሰለቶችን ጨምሮ ዘመናዊ የዓሳ ማስገሪያ መሳሪያዎች ፣ ጀልባዎችና ቀዝቃዛ ሰንሰለት የተገጠመላቸው የተሽከራካሪ ግብዓቶች የተሟሉለት መሆኑ ተገልጿል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በክልሉ በሚገኙ ወንዞችና ሐይቆች 113 ያህል የተለያዩ የዓሳ ዝርያዎች ያለበት አካባቢ ቢኾንም ዘርፉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለመደገፉ በተፈለገው ልክ ሀብቱ ጥቅም ላይ እንዳልዋለ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከለውጡ ወዲህ የዓሳ ሀብትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ለክልሉ ብሎም ለሀገር ኢኮኖሚ ለማዋል ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ መኾኑን ተናግረዋል።

ለዚህም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ድጋፍ ተገንብቶ በዛሬው ዕለት ለአገልግሎት የተዘጋጅው ዘመናዊ የዓሳ ማቀናበሪያና የግብይት ቴክኖሎጂ ማዕከል ዋነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በክልሉ ያለውን የዓሳ ሀብት ልማት በማዘመን ሀብቱ ለክልሉ ብሎም ለሀገር ጥቅም እንዲውል ላደረገው የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ምሥጋና አቅረበዋል።

የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድርና የዓሳ ፕሮጀክቱ ስትሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተንኩዋይ ጆክ የጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በኢታንግና በአበቦ ወረዳ የተገነቡት የዓሳ ፕሮጀክቶች ከ99 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገባቸው ተናግረዋል።

ተመርቆ ለአገልገሎት የበቃው ዘመናዊ የዓሳ ማቀነባበሪያና የግብይት ቴክኖሎጂ ማዕከላት ፕሮጀክት ለአምስት ሺህ ወጣቶች የሥራ እድልን እንደሚፈጥርና ከ12 ሺህ ቶን በላይ የዓሳ ምርት ለማቅረብ እንደሚያስችል ኢዜአ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሀገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የታሪፍ ማሻሻያ መደረጉ ተገለፀ
Next article“ትኩረት በተሰጣቸው የኢንቨስትመንት መስኮች የውጭ ኩባንያዎችን ለመሳብ የሚሲዮኖች ሚና ከፍተኛ ነው” አቶ መላኩ አለበል