
ባሕር ዳር: ጥር 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጤናማ የእናትነት ወር የእናቶችን ጤና ለማሻሻል በሚያግዙ የተለያዩ ተግባራት እንደሚከበር የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ጤናማ የእናትነት ወር በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ17ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ36ኛ ጊዜ ከጥር 1 እስከ ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም “መከላከል በምንችላቸው ምክንያቶች የሚከሰቱ የእናቶች ሞት በጋራ እንግታ” በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እለቱን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓመት ከ295 ሺህ በላይ እናቶች በእርግዝና፣ ወሊድና ድኅረ-ወሊድ ወቅት በሚከሰቱ የጤና ችግሮች ህይወታቸውን እንደሚያጡ ተናግረዋል፡፡
ከዚህም ውስጥ 94 በመቶ የሚሆነው የእናቶች ሞት በታዳጊ አገራት እንደሚከሰት ነው የገለጹት፡፡
በመሆኑም ጤናማ የእናትነት ወር መከበር ዋነኛ ዓላማ የእናቶችን ሕመም እና ሞትን ለመቀነስ በሚደረገው አገራዊ ርብርብ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን ጨምሮ የእናቶችን ጤና ለማሻሻል የሚያግዙ ተግባራት ይከናወናሉ ነው ያሉት፡፡
ወሩን አስመልክቶ በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ የጤና መሰረተ-ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም እና የሕክምና ግብዓቶችና መድኃኒቶችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረው ጎን ለጎንም ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በስፋት ለመሥራት መታቀዱን አብራርተዋል፡፡
የዘንድሮው የጤናማ እናትነት ወር የሚከበረው በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረው ጦርነት ቆሞ ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ ተስፋ ሰጪ ለውጦች በታዩበት ወቅት መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገውም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የእናቶች ሞት ቅኝትና ምላሽ አሰጣጥ ሪፖርት፣ ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ደም ግፊት ኢንፌክሽን እና የደም አቅርቦት እጥረት በኢትዮጵያ ለእናቶች ሞት መንስኤ መሆኑን ያመላክታል፡፡
በዚህም በአገር አቀፍ ደረጃ በየቀኑ 38 እናቶች ከእርግዝና፣ ወሊድና ድኅረ-ወሊድ ወቅት በሚከሰት የጤና ችግር ህይወታቸውን እንደሚያጡ ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።የዘገበው ኢዜአ ነው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!