
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 15/2012 ዓ.ም (አብመድ) ደም በመለገስ በደም መፍሰስ ችግር ሕይወታቸውን የሚያጡ ሰዎችን መታደግ እንደሚገባ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ምክትል ሊቀ መንበርና የማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው አሳሰቡ፡፡
አንድ ሰው ካለው አጠቃላይ ደም እስከ 10 በመቶ ቢለግስ በጤናው ላይ ችግር እንደማያስከትልበት ደግሞ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡
የአዴፓ ምክትል ሊቀ መንበር እና የማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው እንደተናገሩት ደም በመለገስ በተለያዩ አደጋዎች ደም በመፍሰስ ሕይወታቸውን የሚያጡ ወገኖችን መታደግ ይገባል፡፡ ‹‹በግንዛቤ እጥረት ችግር ካልሆነ በስተቀር ማኅበረሰቡ ሁሉን ነገሩን የሚሰስት አይደለም›› ያሉት አቶ ዮሐንስ በደም ልገሳ የሚታየውን የግንዛቤ ችግር ለመቅረፍም ከጤና ተቋማት ባለፈ በማንኛውም ቦታ በኃላፊነት የሚገኝ ሁሉ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የግንዛቤ ችግሩን ለመቀረፍ ተከታታይነት ያለው ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም ነው አቶ ዮሐንስ ቧያለው ያስገነዘቡት፡፡ ‹‹የደም ልገሳን ባሕል ለማድረግ ከዘመቻ ሥራ ወጥቶ በመደበኛነት በትኩረት መሠራት አለበት›› ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡ የደም ልገሳን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ከሌሎች ተግባራት ጋር በመደበኛነት አቀኛጅቶ መሥራት እንዳለበትም ነው አቶ ዮሐንስ ያሳሰቡት፡፡
በክልሉ በደም ባንክ ማዕከላት እና በዘመቻ ደም እንደሚሰበሰብ የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታውቋል፡፡ በቢሮው የድንገተኛ የፅኑ ሕሙማን እና የደም ባንክ አገልግሎት ኬዝቲም አስተባባሪ አቶ አንዳርጌ አጥናፍ እንደተናገሩት ፈቃደኛ ደም ለጋሾች በየሦስት ወሩ በደም ባንኮች እንዲለግሱ ቢፈለግም በማዕከላቱ የሚሰበሰበው ደም 10 ከመቶ አይሞላም፡፡ የማኅበረሰቡ ግንዛቤ ውስን በመሆኑ 90 በመቶ የሚሆነው ደም የሚሰበሰበው በዘመቻ መሆኑንም ነው አስተባባሪው የገለጹት፡፡
‹‹ደም ከበጎ ፈቃደኞች በአራቱ ደም ተህዋስያን አማካኝነት ከሚተላለፉ በሽታዎች ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ተረጋግጦ ይሰበሰባል፡፡ የተሰበሰበውም ያለምንም ብክነት ለሕይወት አድን ተግባር ይውላል›› ብለዋል አቶ አንዳርጌ፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት መስፈርትን ጠቅሰው እንዳብራሩትም በአንድ ሀገር ወይም ክልል ከሚኖረው ሕዝብ ከ1 እስከ 3 በመቶ የሚሆው ደም መለገስ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህም መሠረት ከአማራ ክልል ሕዝብ ከ200 ሺህ አስከ 600 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰብ እንደሚቻል አመልክተዋል፡፡ ይሆን እንጅ የማኅበረሰቡ የደም ልገሳ ባሕል ዝቅተኛ በመሆኑ በሩብ ዓመቱ በክልሉ 10 ሺህ 509 ዩኒት ደም ብቻ ነው መሰብሰብ የተቻለው፡፡
ማንኛውም ጤነኛ የሆነ በጎ ፈቃደኛ ሰው ካለው አጠቃላይ ደም እስከ 10 በመቶ ቢለግስ በጤናው ላይ የሚያመጣበት ምንም ዓይነት ጉዳት እንደሌለም ነው አቶ አንዳርጌ የተናገሩት፡፡
በክልሉ የሚገኙ የጤና ተቋማት የደም ፍላጎታቸውን በአራቱ የደም ዓይነቶች በየጉድኝታቸው (በየክላስተራቸው) ለሚገኙ 10 የደም ባንኮች እንደሚያቀርቡና የተሰበሰበው ደም በፍትሐዊነት እንደሚሠራጭም አቶ አንዳርጌ አመልክተዋል፡፡
በክልሉ በመኪና አደጋ፣ በወሊድ፣ በኩላሊት እጥበት፣ በካንሰር፣ በቀዶ ጥገና፣ በደም ማነስ እና በመሳሰሉት በሽታዎች ምክንያት ደም የሚፈሳቸውን ወገኖች ሕይወት ለመታደግ ማኅበረሰቡ ደም መለገስ እንዳለበትም አቶ አንዳርጌ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
‹‹ሕይወት ለሕይወት፤ ደም ለግሰን ሕይወት እናድን›› በሚል መሪ ሐሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀምበር ከ10 ሺህ ዩኒት በላይ ደም፣ በአማራ ክልል ደግሞ 3 ሺህ 748 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታውቋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ