
ባሕር ዳር: ጥር 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ምዕራብ ጎንደር ዞን እንደ ሰሊጥ፣ ጥጥ፣ ዕጣንና ሙጫ የመሳሰሉ ገበያ ተኮር ምርቶች የሚመረቱበት ዞን ነው። ዞኑ ካለው 760 ሺህ ሄክታር መሬት የሚጠጋ የደን ሽፋን ውስጥ 30 በመቶው በዕጣን ዛፍ የተሸፈነ ነው።
ታዲያ ይሕ ሀብት ተገቢውን ጥቅም ሳይሰጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ እንደሚገኝ ነው በዞኑ በዕጣንና ሙጫ ማምረት የተሠማሩ ማኅበራት የነገሩን።
በመተማ ወረዳ ሌንጫ ቀበሌ ዕጣንና ሙጫ ማምረት ላይ የሚገኘው የአዲስ ሕይወት ኅብረት ሥራ ማኅበር ሊቀመንበር በየነ ውቤ እንዳሉት ማኅበሩ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን በማሰባሰብ ዕጣንና ሙጫ ማምረት ላይ ይገኛሉ። ከዚህ በፊት ለሰሊጥ ምርት ትኩረት በመሰጠቱና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ዕጣንና ሙጫ ምርት ትኩረት ተነፍጎት እንደነበር ነው የነገሩን።
ይኹን እንጅ የሰሊጥ እና የሌሎች ሰብሎች ምርታማነትና የገበያ ሁኔታ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ ፊታቸውን ወደ ዕጣንና ሙጫ ማምረት እንዲያዞሩ አስገድዷቸዋል። ማኅበሩ በ2014 ዓ.ም ለኩንታል 23 ሺህ ብር በመሸጥ 4 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ችሏል፡፡ 680 ሺህ ብር ለመንግሥት መደበኛ ግብር መክፈሉን አንስተዋል፡፡ በዚሕ ዓመት 8 ሚሊዮን ብር ለማግኘት እየሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማኅበረሰቡ የሀብቱን የኢኮኖሚ ጠቀሜታ በመረዳቱ ጥበቃ እያደረገ መኾኑን አንስተዋል። መንግሥትም ትኩረት ሊሠጠው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
በምዕራብ ጎንደር ዞን አካባቢና ደን ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የአካባቢ ሕግ ተከባሪነትና የአካባቢ ማኅበረሰብ ተጽዕኖ ግምገማ ቡድን መሪ ሀብታሙ አድጎ ምዕራብ ጎንደር ዞን ካለው 760 ሺህ ሄክታር መሬት የሚጠጋ የደን ሽፋን ከ234 ሺህ በላይ የሚኾነው በዕጣን ዛፍ የተሸፈነ ነው።
ታዲያ ይህ ሀብት ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በሚጠበቀው ልክ ጥቅም ላይ አለመዋሉን ነው ባለሙያው ያነሱት።
👉በ2014 በጀት ዓመት በዞኑ በተሠራው ሥራ ከ4 ሺህ 70ዐ በላይ ኩንታል ዕጣንና ሙጫ ማምረት ተችሏል።
👉ከ67 ሚሊዮን 134 ሺህ ብር በላይ ደግሞ ገቢ ተገኝቷል።
👉ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት የሮያሊቲ ክፍያ ገቢ ተደርጓል። ገቢው በአካባቢው ከሚመረቱት ገበያ ተኮር ምርቶች ዋጋ ከፍተኛ ልዩነት በማሳየቱ በ2015 ዓ.ም 22 ማኅበራትና 24 ባለሃብቶች በዕጣንና ሙጫ ማምረት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ ገብተዋል።
በዞኑ በዕጣንና ሙጫ ማምረት የተሰማሩ ማኅበራት ለ6 ሺህ ዜጎች በቋሚነት የሥራ እድል ፈጥረዋል። ከዚህ ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች በጊዜያዊነት የሥራ እድል ተፈጥሯል።
በዚህ ዓመት ወደ ሥራ በገቡ 24 ባለሃብቶች ደግሞ ከ3 ሺህ 200 በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት፣ ከ850 በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ በጊዜያዊነት የሥራ እድል ይፈጠርላቸዋል።
ምንም እንኳ ዞኑ ዕጣንና ሙጫ አምራች ቢኾንም እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ ባለመቻሉ ከሀብቱ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እየተገኘ አለመኾኑን አንስተዋል። ሀብቱን እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ ቢቻል ገቢውን በእጥፍ ማሳደግ እንደሚቻል ነው ባለሙያው የገለጹት።
👉በዞኑ ያለውን ዕጣንና ሙጫ በሙሉ አቅም ማምረት ቢቻል በዓመት 35 ሺህ ኩንታል ዕጣንና ሙጫ ምርት ማግኘት ይቻላል።
👉ይሕም አኹን ባለው ዋጋ ለገበያ ቢቀርብ 609 ሚሊዮን ብር ዞኑ ገቢ ማግኘት ይችላል። ከዚህ ደግሞ መንግሥት 121 ሚሊዮን 800 ሺህ ብር የሮያሊቲ ክፍያ ማግኘት ይችላል ማለት ነው።
የዕጣንን ዛፍ ከመጥፋት ለመታደግ ምን እየተሠራ ነው?
የዕጣን ዛፍ አገልግሎት ለመስጠት ረጅም ጊዜ ይወስዳል፤ ራሱንም በጊዜ የሚተካ ዛፍ አይደለም፡፡ ዛፉ ለበሽታ፣ ለቃጠሎ፣ ለነፋስና ለተለያዩ ችግሮችም የተጋለጠ ነው፡፡
👉የዕጣን ዛፍ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ በዘመናዊ ማምረቻ መሣሪያ እንዲመረት ተደርጓል። ባለሙያዎችም የአመራረት ሂደቱን ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
👉ሕገ ወጥ እርሻ መስፋፋት፣ ሰደድ እሳት እና ከሌሎች ችግሮች ለመከላከል የጥበቃ ሥራ ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡ በተለይም ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዋጋው እየጨመረ በመምጣቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ ጥበቃ እየተጠናከረ መጥቷል።
👉የተለያዩ ድርጅቶችም ዘር በማቅረብ፣ ደን ቦታዎችን በመለየት እና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎችን እየሠሩ ነው፡፡
በዞኑ የሚመረተውን ዕጣንና ሙጫ ምርት እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ ምን እየሠራ እንደሚገኝ በዞኑ ለሚገኘው የቴዎድሮስ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ግብይት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየን ጥያቄ አቅርበናል። የዩኒየኑ ሥራ አስኪያጅ ክንዱ ወርቁ በዚህ ዓመት የመጋዘንና የቢሮ ግንባታ ሥራዎችን በመሥራት በ2016 ዓ.ም እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዩኒየኑ እየሠራ እንደሚገኝ ምላሽ ሰጥተውናል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!