
በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ
በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ…“
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የገና በዓል በሚል በስፋት ይታወቃል፡፡
ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የገና በዓል ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገርም የራሱ ብዙ ባሕላዊ እና ትውፊታዊ ገጽታዎችም አሉት፡፡ የገና በዓል ሲደርስ የገና ጨዋታ ይታወሳል፡፡ ጨዋታው አዝናኝና ተወዳጅ ነው፡፡የገና ጨዋታ በሀገራችን ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው፣ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ጨዋታ እንደኾነ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
ከገጠር እስከ ከተማ ወጣቶችና ጎልማሶች የሚያዘወትሩት ተወዳጅ ጨዋታ ነው ፡፡ በጨዋታ ወቅት አዛውንቶችም ከሜዳው አይጠፉም ፣ ጨዋታውን መርቀው ከመክፈትም ባሻገር አልፎ አልፎ የሚጫወቱም አሉ፡፡
በገና በዓል በተለይ ወንዶች በሜዳ ላይ የገና ግጥሚያ ያደርጋሉ፣ሴቶችን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ጨዋታውን ይታደማሉ። በጨዋታው የሚዜመው ግጥም ሥርዓትን እስከ ኹናቴው ሲዘግብ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡
“…አሲና በል አሲና ገናዬ
በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ
በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ…“ ከአይረሴዎቹ የገና ጨዋታ ግጥሞች የሚመዘዙ ስንኞች ናቸው፡፡
ለመኾኑ” በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ ፣በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ”
የሚሉት የገና የጨዋታ ግጥም ሥንኞች ስለ ጨዋታው እና ሁነቱ ምን ይነግሩናል?
በዚሁ ጉዳይ ለአሚኮ ኦንላይን ሚዲያ ሙያዊ ሃሳባቸውን ያጋሩት በአማራ ክልል ባሕል ቱሪዝም ቢሮ የባሕል እሴቶች ልማት ባለሙያዋ አዲሴ አክሊሉ እንደሚሉት የግጥም ስንኞቹ ከጨዋታ የተሻገረ ትርጉም ያለው አስትምኽሮን ይናገራሉ ይላሉ።
“በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ ፣በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ”ማለት በጨዋታው ወቅት የበላይና የበታች፣ አለቃና ምንዝር የሚባሉ ልዩነቶችን የማያስተናገድ ፣በነጻነት የሚከወን ነው የሚል ትርጉም ነው ያለው ባይናቸው።
ለጨዋታ የተገኙት ሁሉ በሜዳ ላይ እኩል ናቸው ይሉናል፤ ባለሙያዋ ግጥሙ የገና ጨዋታ እኩልነትን፣ ፍትሕን እና ለዓላማ ተገዥነትን ፣ነጻነትንም ጭምር የሚያስረዳ ትውፊት ነው ይሉታል።
በየደረጃው የተገኘ ሁሉ ሜዳው ላይ እኩል ይጫወታል ፣ይገፋል ፣ይታገላል፣ይወድቃል ይነሳል እንጂ ጌታ ስለኾነ የተለየ ክብር አይደረግለትም ፤ ሎሌ ስለኾነም የተለየ ነገር አይደረግበትም። እናም ይኽ ባሕላዊ ጨዋታ ትውፊቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲሻገር የዘርፉ ምሁራን ፣መገናኛ ብዙሐንም ኾኑ መንግሥት ትኩረት አድርገው መሥራት እንደሚገባቸውም ነው ያስረዱት።
የገና ጨዋታ መቻቻልን ፣ፍቅርና አንድነትን የሚያስረዳ ፋይዳ ያለው ስለመኾኑም ያስረዳሉ ባለሙያዋ።
በሁለት ጎራ የተሰለፉ ተጋጣሚዎች በተመረጠው አቅጣጫ መሰረት ቦታ ቦታቸውን ይይዛሉ። ጨዋታው ተጀምሮ አቅጣጫውን ያልለየ ተጫዋች ካለ፣ “ሚናህን ለይ›› ተብሎ፣ በገናው ቸብ ሊደረግ ይችላል፤ እርግጫም ጉስሚያም ከተቃራኒ ቡድን ሊገጥመው ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ታድያ ለምን ተመታሁ ተብሎ ኩርፊያም ኾነ ጠብ የለም፡፡
በገና ጨዋታ የተጎዳ፣ ተመቶ የቆሰለ በጨዋታው ሕግ መሠረት አይጠየቅም፤ የጨዋታው ባሕርይ ነውና ይሉታል፡፡
ለዚህም ነው“… በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ…“ የሚባለው፡፡
የገና ጨዋታ ከጨዋታው፣ከመዝናናቱም በዓሉን አስቦ ከመዋልም የተሻገረ ማኅበራዊ ፋይዳው የላቀ ነው ፡፡
በጉዳዩ ላይ በአንድ ወቅት ለአሚኮ ሃሳባቸውን ያጋሩት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁሩ ፈንታሁን አየለ (ዶ.ር) የገና ጨዋታ ባሕላዊ ሥርዓት በጨዋታው የኀብረተሰቡ በአንድነትና በፍቅር መኖርን ፣ እኩልነትን ፣ለሕግ ተገዥነትና መከባበር የሚታይበት ሁነት ነው ይሉታል፡፡
የታሪክ ምሁሩ ዶክተር ፈንታሁን ይህ ሁሉ ፋይዳው እየተዘነጋ ነው ይላሉ፡፡ አሁን ላይ ያ ዘመናትን የተሻገረ ገፀ-ብዙ ማኅበራዊ ፋይዳ ያለው የገና ጨዋታ በወጣቶቹ ዘንድ ትኩረት አጥቷል ነው የሚሉት፡፡
ወጣቶች በፈረንጅ ባሕል እየተጠለፉ ነው ፣የገና በዓል ሲመጣ ከገና ጨዋታ ይልቅ ምንነቱን ባልተረዳው የገና ዛፍ መድመቅን የሚያስቀድም ትውልድ እያየን ነው ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡
የገና ጨዋታ አለቃን ከምንዝር ፣ጌታውን ከሎሌ ፣ሃብታምን ከድሃ ፣አዋቂን ከልጆች በአንድ ሜዳ እኩል የሚያስተናግድ ሁነት ፣የላቀ ማኅበራዊ ፋይዳ ያለው ባሕል ነውና ሊጠበቅ ፣ሊከበርና ለትውልድም ማሻገር ተግባሩ ላይ መሥራት እንደሚገባ ነው የሚያሳስቡት፡፡
እርግጥ ነው በገና ጨዋታ ሜዳ ላይ የሃብት ደረጃን፤ የሥራ ኀላፊነትና ሌሎች ልዩነቶች ሳይኖሩት ሁሉንም ሰው እኩል የሚያሳትፍ የጨዋታ አይነት ነውና “በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ” የጨዋታው ስንኝ ምስክር ነው።
የገናን ጨዋታን ከኢየሱስ ክርስቶስ ውልደት ጋር በማቆራኘት “የኢየሱስ መወለድም የሰውን ልጅ እኩልነት ለማወጅ፣ ኃጢያተኞችን ይቅር በማለት ከሌላው ጋር ያዋኽደ ክስተት በመኾኑ፣ በገና ጨዋታም አሽከርና ጌታው እኩል ይጫወታሉ፤ ሲሉ የሚያብራሩም አሉ፡፡
በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ ነውና የጨዋታው መርኾ ፣ በጨዋታው ላይ በሚደርስ ጉዳትም ኾነ ግጭት ቂምና በቀል በገና ጨዋታ አይታሰብም፡፡
ከጨዋታው በኋላ መብል መጠጡ ተሰናድቶ፣ ድግሥ ላይ ጌታውም ሎሌውም በጋራ እኩል ይበላል ይጠጣል፡፡
መልካም የገና በዓል፣መልካም የገና ጨዋታ!
ዘጋቢ፡-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!