
ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በየዓመቱ የመከበሩ ምክንያት በናፍቆት ሲጠበቅ የነበረው የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ነው፡፡ አዳም እና ሔዋን እጸ በለሥን በልተው ከገነት ከወጡ ጊዜ ጀምሮ ሰው እና እግዚአብሔር በቦታ እና በአስተሳሰብ ተለያይተው ቆይተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የቴሌቪዥን ጣቢያ አዘጋጅ የኾኑት መምህር መጋቢ ብሉይ አዕምሮ ዘውዴ፤ የበዓሉን መከበር ምክንያት ሲናገሩ በናፍቆት ሲጠበቅ የቆየው የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ነው ብለዋል፡፡
አዳም እና ሔዋን እጸ በለስን በልተው ከገነት በተባረሩ ጊዜ አጥብቀው አዝነው ተክዘውም ነበር፡፡ ሀዘናቸውን የተመለከተው እግዚአብሔር አንድ ተስፋ ሰጣቸው፡፡ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሐለሁ የሚል የተስፋ ቃል፡፡ ይኽን ቃል መላዕክት ሰምተዋል፡፡ የሰሙት መላዕክት ለነቢያት ነገሯቸው፡፡
ትንቢት የተነገረለት ሱባኤ የተቆጠረለት ኢየሱስ ክርሥቶስ አዳምን ከፍዳ ከመከራ ያድነው ዘንድ በሥጋ ተወለደ፡፡ እወለዳለሁ ብሎ ሥለመወለዱ፣ እሰቀላለሁ ብሎ ሥለመሰቀሉ፣ እሞታለሁ ብሎ ሥለመሞቱ የተናገረው አምላክ መቸ እንደሚወለድ፣ ከማን እንደሚወለድ፣ አስቀድሞ የተናገረው ኢየሱስ ክርሥቶስ ቃሉ ይፈጸም ዘንድ በሥጋ ተገለጠ፡፡ የተናገረው 5 ሺህ 500 ዘመን ሲፈጸም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ተወለደ ብለዋል፡፡
መምህር መጋቤ ብሉይ አዕምሮ የበዓሉን መከበር ሲናገሩ በዓሉ ለመከበር ብዙ ምክንያት አለው፡፡ በዓሉ የሚከበረው የኹሉም በዓል መጀመሪያ፣ የበዓላት ኹሉ ራስ በመኾኑ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ተሠቀለ፣ ሞተ፣ ተነሣ፣ እና ዐረገ ለማለት መጀመሪያ ተወለደ ማለት የግድ ሥለኾነ ነው ብለዋል፡፡ ከመወለዱ በፊት ትንቢት ተነግሮለታል ሱባኤ ተቆጥሮለታል፡፡ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገለጠ፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ዓለም አዲስ ምዕራፍ እንዲጀምር አድርጎታል፡፡
ሰው እና እግዚአብሔር ፣ሰው እና መላዕክት፣ ነፍስ እና ሥጋ፣ በነገድ በጎሳ ተለያይተው የነበሩት ሕዝቦች ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በዓሉ ይከበራል ብለዋል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ የዓለም ታሪክ በሁለት ተከፍሏል፡፡ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ እና ድህረ ልደተ ክርስቶስ አስብሎታል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚኽች ምድር ሲመጣ አዲስ ምዕራፍ አዲስ ታሪክ ተፈጠረ፡፡
የበዓሉ መከበር ብዙ ጥቅም እንዳለውም መጋቤ ብሉይ አዕምሮ ተናግረዋል፡፡ ልደት የጥምቀት፣ የሥቅለት፣ የትንሳኤ፣ እና የዕርገት በዓላት መነሻ ነው፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ብዙ ነገሮች ተገኝተዋል፡፡ ተጣልተው የነበሩ ሰው እና እግዚአብሔር የታረቁበት ፣ሰላም የተገኘበት ነው ብለዋል፡፡ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለት ቁጥር 11 ላይ “ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባል በምድርም ሰላም” ብለው መላዕክት አመስግነዋል፡፡ ኢየሱስ ክርሥቶስ ሲወለድ ሦስት ነገሥታት ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤ ለማበርከት የመጡት ከሩቅ ምስራቅ እና ከኢየሩሳሌም ቢኾንም በአንድነት ምሥጋና አቅርበዋል ብለዋል፡፡
ተለያይተው የነበሩ አካላት በአንድነት የዘመሩበት የጠፋው ሰላም የተገኘበት ሰው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የቀረበበት፣ ተጣልተው የነበሩ ሰብዓ ሰገል እና እስራኤላውያን የታረቁበት እና ሥጦታ ያቀረቡበት በዓል በመኾኑ ጥቅሙ ብዙ ነው ብለዋል መጋቢ ብሉይ፡፡ በዓሉ ሲከበር የተጣላ ይታረቃል፣ የተራራቀ ይገናኛልም ነው ያሉት፡፡
ዛሬም በዓሉ ሲከበር የተጣላ ይታረቃል ፤የተለያዬ ይገናኛል ፤ተለያይተው የነበሩ ወንድማማቾች ወደ አንድ የመጡበት በመኾኑ ይኽ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!