
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ካህኑ ቅዱስ እና ንጉሥ ላሊበላ ያነጸው የዋሻ ውስጥ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትን ብቻ አልነበረም፤ ትውልድን እና ሀገርን ጭምር እንጂ፡፡ ለአራት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ሰማይ ስር በዘለቀው ሰላማዊ የንግሥና ዘመኑ ሥርዓት አጽንቷል፣ ግብረ ገብነትን አሳይቷል፣ ከምንም በላይ ደግሞ ዘመንን ተሻጋሪ፤ ትውልድን አኩሪ ሀገር ገንብቶ አቆይቷል፡፡
እግዚአብሔር አብ ለሊቀ ነቢያት ሙሴ ዐስርቱን ትዓዛዛተ ኦሪት በሲና ተራራ በድንጋይ ላይ ጽፎ እንደሰጠው ሁሉ ቅዱስ ላሊበላም ከአንድ ዓለት 11 አብያተ ክርስቲያናትን ያንጽ ዘንድ ጸጋ ተሰጠው፡፡ እርሱ በድንኳን እየኖረ የፈጣሪውን ማደሪያ ያሳመረ፤ ስለምጽዋት ሲል የላስታ ዘመን የመጨረሻ ንጉስ የነበረውን ልጁን ይትባረክን ለመስዋዕትነት ያቀረበ ቅዱስም፤ንጉስም እንደነበር በገድሉ ይነገራል፡፡
ቅድስናን ከንግሥና፤ ቤተ ክህነትን ከቤተ መንግሥት አስተናብረው መምራት ከቻሉ ቀደምት ኢትዮጵያዊያን መካከል ቅዱስ እና ንጉስ የሆነው ካህኑ ላሊበላ አንዱ ነው፡፡ ልደቱ በፈጣሪው የልደት ቀን የገጠመለት ቅዱስ ላሊበላ ክርስቶስ በቤተልሄም ሲወለድ በጎች እስትንፋሳቸውን ለሙቀት እንደለገሱት ሁሉ ህጻኑ ላሊበላም እንደተወለደ በንብ መንጋ ተከበበ፡፡
“ንብ ጸጋውን ዐወቀ” ሲሉ ሥሙን ላሊበላ አሉት ይሉናል፡፡ ላሊበላ የሚለው የመጠሪያ ሥሙ ትርጓሜም ከከበቡት ንቦች ጋር የተያያዘ እንደሆነ ከ800 ዓመታት በላይ እድሜ እንዳለው የሚነገርለት ገድለ ቅዱስ ላሊበላ ያሳየናል ይላሉ ሊቃውንተ ቤተ ከርስቲያን ሲናገሩ፡፡
የላሊበላ ተስፋው እግዚአብሔር ነበር ያሉን የቅዱስ ላሊበላ ገዳም አራቱ ጉባኤያት አገልጋይ ሊቀ ጉባኤ ሃብተ ማርያም ባየ ከልጅነት እስከ ዕውቀት፤ ከስደት እስከ ትምህርት፤ መራር ፈተናን ተስፋ አስቆራጭ ችግርን ሁሉ አልፏል ይላሉ፡፡ ነገር ግን ሁሉን በሚችል ፈጣሪው ሁሉን አልፎ ለቅድስና የበቃ ኢትዮጵያዊ ቅዱስም ንጉሥም ነበር ይላሉ፡፡
ሊቀ ጉባኤ ሃብተ ማርያም ቅዱስ ላሊበላ በበርካቶቹ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የሚታወቀው በክህነቱ እና ቅዱስነቱ እንዲኹም ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ግንባታ ጋር በተያያዘ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ንጉስ ላሊበላ ኢትዮጵያ በዘመኗ ካሳለፈቻቸው በሳል ነገሥታት መካከል አንዱ ነበር ይላሉ፡፡ ከሁሉም በላይ የሚጠቀሰው የቅዱስ ላሊበላ ዘመነ ንግሥና ሰላማዊ እና ፍጹም የተረጋጋ እንደነበር ይጠቀሳል፡፡
ከጳጳሳት ሹመት እና ከዓባይ ወንዝ ሙላት ጋር ተያይዞ የቅዱስ ላሊበላ ሥም እስከ ካይሮ ዘልቆ ይታዎቃል የሚሉት ሊቀ ጉባኤ ሐብተ ማርያም በንጉስ ላሊበላ ዘመነ ንግስና፤ ኢትዮጵያ ውጫዊ ግንኙነቷ ጠንካራ እንደነበር ገድለ ቅዱስ ላሊበላ ይናገራል ነው ያሉት፡፡ አብያተ ክርስቲያኖቹ ብቻ ሳይሆን ሥመ-መንግስቱም አሻራው አሁንም ድረስ አልጠፋም፡፡
ቅዱስ ላሊበላ ንግሥናውም ቅድስናውም፤ በሰውም በፈጣሪውም እንክን የሌለበት መሪ እንደነበር ይነገራል፡፡ በነገሠ በ10ኛው ዓመት በ1167 ዓ.ም ገደማ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱን ማነጽ ከመጀመሩ በፊት አሁን አብያተ ክርስቲያናቱ ያረፉበት ቦታ ቀይት የምትባል የአንዲት ባላባት መሬት ነበር፡፡
ቅዱስ ላሊበላ መሬቱን፤ንግሥናውንም ሆነ ክህነቱን ተጠቅሞ ሰው በድሎ ፈጣሪውን ደልሎ ማለፍ አይፈልግምና ባለርስቷን ለመደራደር ቀረበ ይላሉ ሊቀ ጉባኤ ሃብተማርያም፡፡ ትክ ቦታ ሰጥቶ፣ ካሳ ከፍሎ እና ባለንብረቷን አሳምኖ ቦታውን በፍትህ ተቀብሎ ግንባታ ጀመረ፡፡ ይህም ቅዱስ ላሊበላ ካሳ የከፈለ፤ ሊዝን ያስተማረ ዘመናዊ መሪ ያደርገዋል ይላሉ፡፡
ሊቀ ጉባኤ ሃብተ ማርያም አናጺው ንጉስ ህንጻ ብቻ ሳይሆን ሥርዓትንም ዘርግቷል፤ ፍትህን አስፋፍቷል፡፡ ቀይትም ንጉስ አክባሪ፤ ሕግ ተግባሪ ፤ግብረ-ገቦቹን ኢትዮጵያዊያን ትወክላለች ብለውናል፡፡
ዛሬም ድረስ ከሀገሪቱ አራቱም አቅጣጫ የመጡ ኢትዮጵያዊያን አናጺውን ንጉስ ልደቱን እያሰቡ ያከብራሉ፡፡ የፈጣሪውን ልደት ከልደቱ ጋር ባነጻቸው አብያተ ክርስቲያናት ወገኖቹ ያከብሩ ዘንድ ምክንያት ሆኗልና፤ ቀይት የንጉሷን ልመና ሰምታ መሬቷን ለእግዚአብሔር ማደሪያ ሰጥታለችና “አናጺው ንጉስ ዛሬም ከብረኻል፤ ባለጸጋዋ ቀይትም ተመስግነሻል” እንላለን፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!