
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እምነት እና እውነት፤ ጽናት እና መስዋዕትነት ያቆሟት ሀገር፡፡ በሳል ነገሥታት፤ ሩቅ አሳቢ ሊቃውንት ሕግ መስርተው ሥርዓት አጽንተው ሀገራቸውን ልዩም ምስጢራዊም አድርገዋት አልፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከቀሪው ዓለም ትለያለች ሲባል ማሳያዎቹ የበዙ ናቸው፡፡ የልደት በዓል ክርስቲያኖች 44 የጾም እና የጸሎት ቀናትን አሳልፈው የሚያከብሩት ታላቅ በዓል ነው፡፡ ለ5 ሺህ 500 ዘመናት በጉጉት የተጠበቀው የአዳም የመዳን ቀን በክርስቶስ መወለድ እውን ሆኗልና ክርስቲያኖች ሁሉ ልደቱን በደስታ ያከብሩታል፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ሰው እና መላዕክት ከላይ እና ከታች ሆነው የመጣውን ንጉስ ማንነት ዐወቁ፤ ሰማይ እና ምድር ስለፍቅሩ ታረቁ፡፡ ዓለም የክርስቶስ ልደት የድኅነቷ ምክንያት ነውና በዓሉ ዓለም አቀፋዊ በዓል ሆኖ በየዓመቱ ይከበራል፡፡ ሀገራት በዓሉን ሲያከብሩ የተለያዩ መገለጫዎች ቢኖሯቸውም በጥንቷዊቷ ደብረ ሮሃ በአሁኗ ላሊበላ የሚከበረው የልደት በዓል ግን ከቀሪው ዓለም ይለያል ይባላል፡፡
በላሊበላ ማራኪ እና ልዩ የሆነው የልደት በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚፈጸመው በቤተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ከዓለም የተለየው የላሊበላ ገዳም የልደት በዓል ልዩ ሥርዓት የሚፈጸመው ደግሞ በተለምዶ ማሜ ጋራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው ያሉን በቅዱስ ላሊበላ ገዳም የአራቱ ጉባኤያት አገልጋይ ሊቀ ጉባኤ ሀብተ ማርያም ባየ ናቸው፡፡ ማሜ ጋራ የቤተ ማርያም ተፈጥሯዊ አጥር የሆነ ኮረብታማ አለት ነው፡፡
ከላይ በማሜ ጋራ ዓለት አናት ላይ፤ ከታች ደግሞ በቤተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን መሰረት አካባቢ ካህናት በተለየ ድባብ ዝማሬ እና ዝማሜን ያደርጋሉ፡፡ ይህ ሥርዓት “ቤዛ ኩሉ” ይባላል የሚሉት ሊቁ ፤ ሥርዓቱ ላሊበላ ላይ ብቻ የሚፈጸም እንደሆነም ነግረውናል፡፡
ከ2 ሺህ ዓመታት በፊት በቤተልሔም የክርስቶስን መወለድ አስመልክቶ መላዕክት ከሰማይ እረኞች ከምድር “ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ” ሲሉ በጋራ አመስግነዋል የሚሉት ሊቀ ገባኤ ሀብተ ማርያም ባየ በልደት በዓል ጠዋት ላይ የሚካሄደው የቤዛ ኩሉ ሥርዓትም ይህንን የሚያወሳ ነው ይላሉ፡፡ ማሜ ጋራ አናት ላይ ሆነው የሚዘምሙት ካህናት መላዕክትን፤ ከታች ሆነው የሚያሸበሽቡት ካህናት እረኞችን እንደሚወክሉም ሊቁ ነግረውናል፡፡
ቤዛ ኩሉ ማለት መላዕክት እና እረኞች ከላይ እና ከታች ሆነው መወለዱን ሲያበስሩ የሚያሳይ ሃይማኖታዊ የገዳማቱ ሥርዓት ነው የሚሉት ሊቀ ጉባኤ ሀብተ ማርያም “ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ” ወይም “የዓለም ቤዛ ዛሬ ተወለደ” በማለት ከ2 ሺህ 15 ዓመታት በፊት በቤተልሄም የነበረውን ክስተት በምልሰት የሚያወሱበት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነው ብለውናል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት የልደት በዓል አከባበር ከዋዜማው ጀምሮ የምሽቱ ማሕሌት ተቁሞ የሌሊቱ ቅዳሴ እንዳበቃ የበዓሉ ፍጻሜ ይሆናል፡፡ በላሊበላ ግን በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የሌሊቱ ቅዳሴ ካበቃም በኋላ እስከ ጠዋቱ ሦስት ስዓት ድረስ ቤዛ ኩሉ ይቀጥላል ነው ያሉት ሊቀ ጉባኤ ሀብተ ማርያም፡፡
ከእያንዳንዱ አብያተ ክርስቲያናት 12 የሚደርሱ ካህናት
ያሬዳዊ ዜማ ለማጀብ ይወጣሉ፡፡ ካህናቱ ወደ ቤዛ ኩሉ ሥርዓቱ ሲያቀኑ ከጃኖ እስከ ሸማ፤ ከልብሰ ተክህኖ እስከ ካባ ደርበው በተለየ ድምቀት ይዘልቃሉ፡፡ ቤዛ ኩሉ አንድ ሰዓት የሚጠጋ ጊዜ የሚወስድ እና በካህናቱ እና በእለቱ የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ታዳሚ ምዕመናን እልልታ እና ጭብጨባ ደምቆ ይጠናቀቃል፡፡
እንኳን አደረሳችሁ!
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!