እንኳን ለጌታችንና ለመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

162

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን እንኳን ለጌታችንና መድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ እያለ መልካም ምኞቱን ይገልጣል፡፡

በክርስቲያኖች ዘንድ እንደሚታመነው በኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ምክንያት በአምላካችን እና በአዳም ልጆች መካከል የነበረው የመለያየት ግድግዳ ፈርሶ በምትኩ ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም የወረደበት፣ የምስራች ለምድራችን የተሰጠበት ነው፡፡ በዓለ ልደተ ክርስቶስ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል እርቅ የተፈጸመበት በዓል መታሰቢያ ነው፡፡ ለሞት ከመገዛት ነጻ የተወጣበት፤ ጨለማው ተወግዶ የብርሃን ልጆች የመሆን ስልጣን የተሰጠበት፤ የእባብ ራስ የተቀጠቀጠበት፤ የሰው ልጅ ከመላእክት ጋር ሆኖ ለእግዚአብሔር ምስጋና ያቀረበበት፤ ከነቢያት ኅብረት ጋር አንድነት የተገኘበት በዓል ነው፡፡

የአማራ ክልል ሕዝብ ከመላው ኢትዮጵያዊ ጋር በመሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የደረሰውን ግፍ ለመከላከል ሁሉን አቀፍ ትግል አድርጓል፡፡ ወረራውን ለመቀልበስ ካደረገው ትግል እኩል ኢትዮጵያዊ አንድነት እንዲጠናከርና የአማራ ሕዝብ ከትግራይ ወገኖቹም ሆነ ከመላው ኢትዮጵያዊ ጋር አምላካችን ለሰው ልጆች የሰጠው ሰላም እንዲሰፍን ብዙ ጥረቶችን ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡

ሕዝባችን የሰላም ስምምነቱ ይዞት የመጣውን የሰላም አየር እያጣጣመ ባለበት በዚህ ጊዜ መንግሥታችን በወረራው ምክንያት ሕዝባችን የወደመበትን መሰረተ ልማት ለማሟላት፣ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት፣ የተፈናቀሉ ወገኖቻችን መልሶ ለማቋቋም፣ የተጎዱ ቤተሰቦችን ከጎናቸው ቆመን ለማጽናት ሌላ የትግል ምዕራፍ ተከፍቶ እየተረባረብን ያለንበት ወቅት ነው።

ይህንን በዓል ስናከብር “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶታልና” እንዳለ ወንጌል ክርስቶስን ለሰው ልጆች መድኀኒት አድርጎ የሰጠን አምላካችን እያንዳንዳችን በመዋደድ ለሌላው የፍቅር ስጦታን በመስጠት በዓሉን በአንድነትና በደስታ ማክበር ይገባናል። የተቸገሩትን፣ የተፈናቀሉትን፣ ወገን ዘመድ የተሰዋባቸውን በመርዳት ክርስቶስ ለሰው ልጆች የሰጣት ወደ እርሱም የምታቀርብ ዋነኛዋ “መዋደድ” ወይም “ፍቅር” የተሰኘችዋን ትእዛዝ መተግበር የሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን ተግባር ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖተኛ ሕዝብ እንደመሆኑ በፈጣሪው የሚመካና አምላኩን የሚወድ እንደሆነ ብዙ ቅዱሳት መጻሕፍት የመሰከሩት ሃቅ ነው። ሃይማኖተኛነት የሰላም፣ የመረዳዳትና የመከባበር እንዲሁም የመዋደድ ፀጋ የሚያላብስ ከመሆኑ በላይ “አንተንም ለሚወድዱ ልማት ይሁን።” እንዳለ ቅዱስ መጽሐፍ ሠርቶ መበልጸግ፣ ለምቶ ለሰው መትረፍ የመንግሥታት ሥራ ከመሆኑም በላይ የሃይማኖተኞችም ትልቁ ድርሻ ነው።

የአማራ ክልል መንግሥት በጦርነቱ የደረሰበትን የምጣኔ ሃብት ጫና ለመቋቋም ብቻ ሳይሆን ሃገራችን የምትጠብቀውን እድገት ለማሳካት የአንበሳውን ድርሻ በመወጣት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ገበሬዎቻችንን፣ ባለሃብቶቻችንን እና መላው የገጠርና የከተማውን ወጣትና አምራች ኃይል ይዘን በመረባረብ ላይ እንገኛለን። ይህንንም ሕዝባችንን ይዘን እንደምናሳካው እምነታችን የፀና ነው። ስለሆነም የጌታን የልደት በዓል ስናከብር መላው ሕዝባችን አምላካቸውን ለሚወዱ የተገባውን ልማት የእኛ እንዲሆን ለማድረግ የጀመርነውን ልማት ለማሳካት የምናደርገውን ንቅናቄ በመደገፍና ፍጹም ቁርጠኝነትን በማሳየት ጭምር መሆን ይኖርበታል።

የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሁሉም የክልላችን አካባቢዎች በሕዝባችን ከሚከበሩ ዐበይት በዓላት አንዱ እንደመሆኑ በገጠርም ሆነ በከተማ የሚኖረው ሕዝባችን በዓሉን በማክበር ሂደት ከመጠን ባለፈ ደስታና ፈንጠዝያ ራስን ለአደጋ ከማጋለጥ በመቆጠብ፣ ሁሉንም በልኩ በማድረግና አቅመ ደካሞችን በመደገፍና በማገዝ የጋራ ደስታ በመፍጠር መሆን ይኖርበታል።

የበዓላት ወቅት ከፍተኛ የሆነ የገበያ እንቅስቃሴ፣ የሰው ፍሰት እና ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ ሃይል አጠቃቀም የሚታይበት እንደመሆኑ በሁሉም የክልላችን አካባቢዎች የሚገኘው ሕዝባችን በዓሉን በኃላፊነት ከማሳለፍ ጎን ለጎን ያለምንም የፀጥታ ስጋት ማክበር እንዲችል ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ያስፈልጋል። ሕዝቡ በግብይት ወቅት ሊከሰት ከሚችል የማታለል እና ማጭበርበር ወንጀሎች ራሱን ከመጠበቅ በተጨማሪም ወንጀሎች ሲከሰቱ እና አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ መረጃዎችን በመስጠት ከፀጥታ ኀይሉ ጎን በመሆን የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ስናከብር ከእርሱ ዘንድ የተሰጡንን በይቅርታ በመታደስ፤ በፅኑ ቃል በመጠበቅ እና ከፍቅር በመነጨ ሰላም ዛሬያችንን በመዋጀት እንዲሆን መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡

እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ!

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ
ባሕር ዳር

Previous article“ጠጥቶ ማሽከርከር የበዓላት ወቅት ዋነኛ የአደጋ መንስዔ ነው” ኮማንደር ሙሉጌታ በዜ
Next article“ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ”