“ጠጥቶ ማሽከርከር የበዓላት ወቅት ዋነኛ የአደጋ መንስዔ ነው” ኮማንደር ሙሉጌታ በዜ

134

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በበዓላት ወቅት ከደማቅ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች በተጨማሪ በጋራ መብላት እና ሰብሰብ ብሎ መዝናናት የተለመደ ነው። በተለይም ወጣቶች ከቤት ወጣ ብለው ለመዝናናት መጠጥን ያዘወትራሉ። ለወትሮው የመጠጣት ልምዱ የሌላቸውም ጭምር የበዓላት ወቅት ግን “የዛሬን ብቻ” በሚል ብሂል ከልምዳቸው እና ከአቅማቸው በላይ ሲጠጡ ይስተዋላል።

ይህ የማይመከር ቢኾንም በዓላትን ለማድመቅ እና ማኅበራዊ መስተጋብርን ለማጠናከር ከኾነ መቅመሱ ባልከፋ ነበር። ከቤት ሲወጣ ወዳጅ ዘመድን ሰብስቦ በተሽከርካሪ ጉዞ በሚኖር ጊዜ ግን መዘዙ ብዙ ነው። “ከጠጡ አይንዱ” የሚለው የጥንቃቄ መልዕክት ይሻርና የራስን እና የወዳጅ ዘመድን ሕይወት የሚያሳጣ አደጋ ሊያስከትል ይችላል።

በአማራ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ሙሉጌታ በዜ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ አሽከርካሪዎች በበዓላት ወቅት ማድረግ ስላለባቸው ልዩ ጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፈዋል።

እንደ ኮማንደር ሙሉጌታ ገለጻ በበዓላት ወቅት በርካታ ማኅበረሰብ ከቦታ ቦታ እንደሚንቀሳቀስ እና የትራፊክ እንቅስቃሴም እንደሚጨናነቅ ገልጸዋል። አሽከርካሪዎች ሙያው የሚፈልገውን ባሕሪ በመላበስ በልዩ ጥንቃቄ ኀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ነው ያሳሰቡት።

በተለይም ጠጥቶ ማሽከርከር የአሽከርካሪዎችን ትኩረት እና ቅልጥፍና ስለሚያሳጣ ለአደጋ ያጋልጣል ብለዋል። ጠጥቶ ማሽከርከር የበዓላት ወቅት ዋነኛ የትራፊክ አደጋ መንስዔ መኾኑንም ጠቁመዋል። ስለዚህ አሽከርካሪዎች የበዓል ደስታን ከሚያጨልም አደጋ ለመራቅ ከመጠጥ ራሳቸውን ማራቅ አለባቸው ሲሉም ገልጸዋል። የሚጠጡ ከኾነም መኪናቸውን እና ቁልፉን ከቤት በማስቀመጥ መኾን አለበት ብለዋል።

ሰብሰብ ብሎ ለመዝናናት ወዳጅ ዘመድ ይዘው የወጡ አሽከርካሪዎች በድንገት መጠጥ ከጠጡ ከማሽከርከር በፍጹም መቆጠብ እንዳለባቸውም ኮማንደሩ ተናግረዋል። የራስን እና የወዳጅ ዘመድን ሕይወት ለሚቀጥፍ አደጋ ስለሚያጋልጥ መኪናውን በተገቢው ቦታ አቁሞ ደኅንነቱ በተጠበቀ ተሽከርካሪ እና አሽከርካሪ መመለስን መምረጥ ይገባልም ነው ያሉት።

ኮማንደር በዜ አሽከርካሪዎች በበዓላት ወቅት ራሳቸው ካለመጠጣትም ባለፈ ጠጥቶ የሚወጣ እግረኛ ሊኖር እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ ከምንጊዜውም በላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል። በተለይም እንደ ጥምቀት ባሉ የጎዳና በዓላት ወቅት ትዕግስት በተሞላበት መልኩ በማሽከርከር በቡድን ወይም በነጠላ የሚያልፋ እግረኞችን ቆሞ ማሳለፍ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ያስተላለፉት መልእክት።
Next articleእንኳን ለጌታችንና ለመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!