
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የባሕርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በመልዕክታቸው በዓሉ የሰላም የፍቅርና የረድዔት በዓል ይኾን ዘንድ ተመኝተዋል፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሁላችንም ልደት ነው ብለዋል ብፁዕነታቸው፡፡ በልደቱ ሰላም የሰፈነበት፣ የራቁ የቀረቡበት፣ የተቅበዘበዙ ሁሉ የተጽናኑበት፣ ሰላም የምሥራች ተብሎ የታወጀበት ሰውና መላእክት በአንድነት የዘመሩበት መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም የኢየሱስ ክርስቶስ ልደትን የዓለም መድኃኒት ተወለደ እያለች እያመሰገነች እንደምታከብረው ገልጸዋል፡፡
በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ ኩነኔ፣ የመከራው፣ የሰቆቃውና የዋይታው ዘመን ያከተመበት፣ የሰላምና የይቅርታ ዓመት የተጀመረበት ነውም ብለዋል፡፡ በአመጽና በሽንገላ ይኖር የነበረ ሕዝብ ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ከአመጽ፣ ከሽንገላና ከአምልኮ በዓድ ተላቆ እግዚአብሔርን እያመሰገነ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሲከበር የተቸገሩትን በመርዳት፣ ያዘኑትን በማጸናናት፣ የታሰሩትን በመጠየቅ ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በዓሉ መንፈሳዊ ሥራ የሚሠራበት እንጂ ባላስፈላጊ ዓለማዊ ምኞትና ሃሳብ የሚታለፍ አለመኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ክርስቲያኖች ሁሉ ሃይማኖቱን የጠበቀ መልካም ሥራ እንዲሠሩም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ሰላምን እንከተላት፣ ሰላምን እንውደዳት፣ ሰላምን እንያዛት፣ ሰላምን ለሌላውም እንስጣት፣ እኛም እንቀበላት ብለዋል ብፁዕነታቸው፡፡ በበዓለ ልደት እግዚአብሔር የሚመሰገንበት መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ ሰላም አጥታ የነበረችው ኢትዮጵያ የሰላም አየር የተነፈሰችበት፣ ከቤትና ከንብረታቸው ርቀው የኖሩት ወደ ቤታቸው ለመመለስ ተስፋ የሰነቁበት፣ የተለያዩ አንድ የኾኑበት የተዘጋው በር የተከፈተበት ነውም ብለዋል፡፡
ለሰላም ግማሽ የለውም ያሉት ብፁዕነታቸው ከሁሉም ነገር ለሰላም ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ከሰላም ውጭ ያለው ነገር ጥቅም እንደሌለውም ገልጸዋል፡፡ ተፋቅሮና ተረዳድቶ መኖርን ገንዘብ እናድርግ፣ ጥላቻን እናርቅም ብለዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደ ስንል ሰላምን ሰጠን፣ በአንድ ላይ እንድንዘምር ፈቀደልን፣ ከእርሱ ጋራ እንድንኖር ጠራን፣ መረጠን እያልን ነውም ብለዋል ብፁዕነታቸው በመልእክታቸው፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!