“የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ስናከብር በፍቅር እና በይቅርታ ይኹን” የአማራ ክልል የሽምግልና ሥርዓት ማኅበር ፕሬዝዳንት ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን

90
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የክረምቱ ለጋ ቡቃያ መስከረም ሲጠባ ያብባል። በጥቅምት ያሽታል፣በኅዳር ይጎመራል። በታኅሣሥ ደግሞ ይደርቅና ይታጨዳል፣ ተወቅቶም ወደ ጎተራ ይገባል። ታኅሣሥ፤ ያረሰ ገበሬ ኹሉ የሥራውን ውጤት አይቶ የሚደሰትበት የፍስሐ ወር ነው። ቂም ኹሉ ከሰው ልጅ ይርቃል፣ በሰበብ አስባብ የተጋጨ ይቅር ይባባላል። በሥራ ተጠምዶ የከረመው ኹሉ በአንድነት ተሰባስቦ አብሮ የሚበላበት እና የሚደሰትበትም ወር ነው ታኅሣሥ።
ይኽ ወር በመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ የኾነው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የሚከበርበት ወር ነው። ታኅሣሥ “የገና ወር” በመባልም ይታወቃል። የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ከሃይማኖታዊ ስርዓቱ በተጨማሪ በተወዳጁ ባሕላዊ የገና ጨዋታ ይደምቃል። የበዓሉን መከበር ተከትለው የሚከናዎኑ የአንድነት እና የመዋደድ ባሕላዊ እሴቶችም የእርስ በርስ ፍቅርን ይጨምራሉ ።
የአማራ ክልል ሽምግልና ሥርዓት ማኅበር ፕሬዝዳንት ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አከባበር ድሮና ዘንድሮ ያለውን መልክ እያነፃጸሩ አጫውተውናል። እንደ ሊቀ ኅሩያን ገለጻ ቀደም ባሉት ጊዜያት የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ወይም በዓለ ገና ሲከበር ያለፈ ቂምን መርሳት እና ይቅር መባባል ተቀዳሚ ተግባር ነበር። በተለይም በቅርጫ ሥርዓት እና ደንብ መሰረት የተጣላ ሰው ይቅር ሳይባባል አብሮ በቅርጫው አይሳተፍም። ሽማግሌዎች የተጣሉ ሰዎችን በማፈላለግ የተበደለን ሁሉ ይቅር አባብሎ በማስታረቅ ይጠመዳሉ።
በታኅሣሥ ወር አዝመራው ተሰብስቦ፣ የመስኩ ሳርም ደርቆ ለገና ጨዋታ ምቹ ስለሚኾን ወጣቶች እና ታላላቆችም ገና ይጫወታሉ። የገና ጨዋታው በጥብቅ ሥርዓት እና ደንብ የሚመራ ሲኾን ማኅበራዊ ግንኙነትን ለመመስረት እና ለማጠናከር ትልቅ ሚና ይጫዎታል።
በኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ቀን ወዳጅ ዘመድ ተጠራርቶ ማዕድ ይጋራል። መጀመሪያ በታላቅነት ከተመረጠው አባውራ ቤት ግብዣው ይደረጋል። በእድሜ ዝቅ ወዳለው ቤት እየወረደ ይቀጥላል። ይሄም ታላቅን የማክበር አንዱ ማሳያ ተደርጎ ይወሰድ ነበር ይላሉ ሊቀ ኅሩያን በላይ የእርሳቸውን የልጅነት ጊዜ እያስታወሱ።
እርሳቸው እንደሚሉት የበዓሉ አከባበር በርካታ እሴቶችን ይዞ የቀጠለ ቢኾንም አንዳንዶች ግን ተቀይረዋል። በዓሉ ሲቃረብ የተጣላን አስታርቆ አብሮ ለማሳለፍ የሚደረገው ጥረት በተለይም በከተማዎች አካባቢ ተቀዛቅዟል ብለዋል። ግለኝነት እየጎላ በመምጣቱ በዓሉን በጋራ ማክበር ላይ መጠነኛ ለውጥ ስለመኖሩ ሊቀ ህሩያን ትዝብታቸውን ገልጸዋል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት ጨፌ ተጎዝጉዞ የሚደምቀው ቤታችን አሁን ላይ ግን ሉላዊነት በፈጠረው ተጽዕኖ በተለይም በከተማ አካባቢ በውድ ዋጋ በሚገዛ መጤ የገና ዛፍ መጥለቅለቁን ሊቀ ኅሩያን ታዝበዋል። ከአለም ተነጥሎ መኖር ባይቻልም ለመሰል መጤ ቁሳቁስ ውድ ዋጋ ማውጣት ግን አላስፈላጊ እንዳልኾነ መክረዋል።
የገና ጨዋታ በገጠሩ አካባቢ እንደቀጠለ ቢኾንም በፊት ይሰጠው የነበረ ትኩረት እና ድምቀት አሁን እንደሌለ ገልጸዋል። ገና ጨዋታ ልክ እንደ እግር ኳስ የራሱ መጫዎቻ ቋሚ ሜዳ ተዘጋጅቶለት አንዱ የቱሪዝም ሃብት መኾን እንዳለበትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሊቀ ኅሩያን በላይ “የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ስናከብር በፍቅር እና በይቅርታ ይኹን” ሲሉ ገልጸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው ለሰው ልጆች ሁሉ አዲስ ሕይወትን ለመስጠት ነው። ስለዚህ በዓሉ በመጣ ቁጥር የተጣላን በማስታረቅ የበደለ ይቅርታ በማለት ከጥላቻ ነፃ መኾን እና ዘላቂ አንድነትን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ላሊበላ እንደ ጎል፤ ሕዝቡም እንደ ሰባ ሰገል!”
Next articleʺተፋቅሮና ተረዳድቶ መኖርን ገንዘብ እናድርግ፣ ጥላቻን እናርቅ” ብፁዕ አቡነ አብርሃም