“ሕዝበ ክርስቲያኑ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ሲያከብር በመረዳዳትና በመተሳሰብ መኾን አለበት” ብፁዕ አቡነ ዲዮናሲዮስ

178
ደብረማርቆስ፡ ታኅሣሥ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሕዝበ ክርስቲያኑ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ሲያከብር በመረዳዳትና በመተሳሰብ እንዲያከብር የምስራቅ ጎጃም ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮናሲዮስ
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ አበይት በዓላት አንዱ የኾነው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በየዓመቱ ታህሳስ 29 ይከበራል።
ነገ ቅዳሜ የሚከበረውን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓል አስመልክቶ የምስራቅ ጎጃም ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምስራቅ ጎጃም ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዲዮናሲዮስ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ኢዮሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን በስጋ የተገለጠበት በዓል ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተራርቆ የነበረውን የሰው ልጅ አንድ ለማድረግ እና ከፈጣሪው ጋር ለማስታረቅ ራሱን ዝቅ አድርጎ ተወልዷልና የኢየሱስ ክርስቶስን አርዓያ በመከተል እርስ በእርስ በመረዳዳትና በመተሳሰብ ልናከብር ይገባል ብለዋል።
በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን በርካታ ወገኖች ተፈናቅለው ሃብት እና ንብረታቸው ወድሞባቸው በመጠለያ ይኖራሉ ያሉት ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ በዓሉም የመረዳዳት በዓል በመሆኑ ሕዝበ ክርስቲያኑ በድንኳን ያሉ ወገኖችን በማሰብ ተደስተው እንዲውሉ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግም አሳስበዋል።
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተጀመረው የሰላም ድርድር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ብፁዕነታቸው ጦርነት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ሀገራችን ላይ ያሳለፍናቸው ጦርነቶች አስረጅ ናቸው። በመሆኑም ኢትዮጵያ እንኳን ለእኛ ለሌሎችም ትተርፋለች አንተ ከዚህ ነህ ፤ ከዚያ ነህ ከመባባል ወጥተን በጋራ እና በአንድነት ልንኖር ይገባል ብለዋል።
በዓሉ ሲከበር መብላት መጠጣት የበዓሉ አንዱ አካል ነው ያሉት ብፁዕ አቡነ ዲዮናሲዮስ ኀብረተሰቡ የኢየሱስ ክርስቶስን አስተምሮ በመከተል በየአካባቢው የሚገኙ የተቸገሩ ወገኖችን ማዕድ በማጋራት በዓሉን ሊያከብር እንደሚገባም መክረዋል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ሀገረ ስብከትም በየአጥቢያ ቤተክርስቲያኑ ተጠልለው የሚገኙ አቅመ ደካሞችና የተቸገሩ ወገኖች በዓሉን በደስታ እንዲውሉ ቅደመ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋ፤ ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ።
ዘጋቢ፦ አማረ ሊቁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበገነት አምሳል የተሰራው ቤተ አማኑኤል
Next article“ላሊበላ እንደ ጎል፤ ሕዝቡም እንደ ሰባ ሰገል!”