
ወልድያ: ታኅሣሥ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ያለ ትርጉም የታነጸ ያለ ምክንያት የተቀረጸ ኪነ-ህንጻ የለም፡፡ ትርጓሜያቸው ረቂቅ፤ ውክልናቸው ምጡቅ የሆኑት የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መሰረታቸው መጽሃፍ ቅዱስ፤ መሪያቸውም መንፈስ ቅዱስ እንደነበር ይታመናል፡፡

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ላሊበላ ያነጻቸው ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት አንዱ ሌላውን አይዎክልም፤ አንዱ አንዱን ፈጽሞ አይመስልም ይላሉ፡፡ በገነት አምሳል የተሰራው ቤተ አማኑኤል የቅዱስ ላሊበላ 9ኛ ሥራው እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከአስራ አንዱ የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ቤተ አማኑኤል በስፋቱ ሁለተኛው ነወ።
ዓለም ከሕንጻ ላይ ሕንጻ እየደራረበ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ መገንባትን ፈጽሞ ባልተዋወቀበት በዚያ ዘመን ቅዱስ ላሊበላ አዲስ የኪነ-ሕንጻ ጥበብ ባለቤት ነበር ያሉን በቅዱስ ላሊበላ ገዳም የአራቱ ጉባዔያት አገልጋይ የሆኑት ሊቀ ጉባኤ ሐብተ ማሪያም ባየ፤ ቤተ አማኑኤል ሦስተኛ ፎቅ ሆኖ የተሠራ ቤተ ክርስቲያን ነው ይሉናል፡፡
እንደ ሊቀ ገባኤ ሐብተ ማሪያም ገለጻ ከቤተ ገብርኤል ተነስቶ ውስጥ ለውስጥ የሚወስድ የጨለማ መንገድ አለ፤ ይህ የጨለማ መንገድ አምሳለ ሲኦልን ይወክላል ይላሉ። ምዕመናኑ ከቤተ ገብርኤል ተነስተው ቤተ መርቆሪዎስ ከደረሱ በኋላ እጅ ነስተው በገነት አምሳል ወደ ታነጸው የቤተ አማኑኤል ውቅር ቤተ ክርስቲያን ይደርሳሉ፡፡
ቤተ አማኑኤል በጽርሐ አርያም አምሳል የተገነባ የገነት ተምሳሌት የሆነ ቤተ ክርስቲያን ነው ያሉት የዐራቱ ጉባዔያት አገልጋይ ቤተ አማኑኤል 9 ክፍሎች አሉት፡፡ በግንባታ ጥበቡ ለተመልካቹ ሳቢ እና ማራኪ የሆነው ቤተ አማኑኤል በ1946 ዓ.ም ካምፖስ እና በ1956 ዓ.ም ደግሞ ሳንድሮ አንጀሊን የተባሉ ጣሊያናዊያን በኪነ-ህንጻው ላይ ጥገናዎችን ማድረጋቸው ቅርሱ ጉዳት ላይ እንዳይወድቅ እንዳደረገው የነገሩን አገልጋዩ አሁንም አስቸኳይ ድጋፍ እና በቂ ክትትል ከሚያስፈልጋቸው አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ እና ዋናው ነው ብለውናል፡፡

የልደት በዓል ሰሞን የተለየ ቀለም ያለው ሥርዓተ ማሕሌት ከሚካሄድባቸው አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ ቤተ አማኑኤል ነው ያሉን ሊቀ ጉባኤ ሐብተ ማሪያም ወረቦቹ ልዩ እና የአካባቢው መገለጫ የሆኑ፤ ከትውልድ ትውልድ ሲወራረዱ የቆዩ በመሆናቸው ዘመን ተሻጋሪ ሆነዋል ይላሉ፡፡
የልደትን በዓል በላሊበላ ለመታደም የመጡ ምዕመናን ዋዜማውን በቤተ አማኑኤል ሊታደሙ ይገባል ያሉት ሊቁ ከዋዜማው ጀምሮ እስከ ሌሊት ድረስ አገልጋዮች የተለያዩ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ስለሚፈጽሙ እንግዶች እንዲገኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!