የአዋሽ ቢሾላ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ምልምል ወታደሮችን አስመረቀ።

254

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአዋሽ ቢሾላ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በዛሬው ዕለት በመሰረታዊ ውትድርና ያሰለጠናቸውን ምልምል ወታደሮች አስመርቋል።

በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የመከላከያ ህብረት የሰው ሃብት አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል ሀጫሉ ሸለመ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ለሠላም ትልቅ ዋጋ የምትሠጥ፣ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ለሠላም መስዋዕትነት የከፈለች ሠላም ወዳድ ሀገር ናት።

የጦርነትን አስከፊነት እና የሠላም ዋጋ ከማንም በላይ የምትረዳው ኢትዮጵያ የጀመረችው የልማት ዕድገት እውን እንዲሆን ቅድሚያ ለሠላም ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ነው ሲሉም ሌተናል ጄነራል ሀጫሉ ሸለመ ገልጸዋል።

የልማት ዕድገታችን እና ሠላማችን እንዲረጋገጥ የአንበሳውን ድርሻ መከላከያ ይወስዳል ያሉት ጄነራል መኮንኑ፤ የገጠሙንን ከፍተኛ የህልውና አደጋዎች በመቀልበስ መከላከያ ሠራዊቱ የበኩሉን ተወጥቷል ብለዋል።

በየጊዜው አጀንዳዎቻቸውን እያቀያየሩ እኛን ለመፈተን ከመሞከር ወደ ኋላ የማይሉ ጠላቶቻችንን ለመከላከል ኢትዮጵያን የሚመጥን የመከላከያ ኀይል የመገንባት ተልዕኳችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

የመከላከያ ኃይል ግንባታን ዘመኑ በሚጠይቀው ልክ በአደረጃጀት፣ በስልጠና እና በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራን በማጠናከር የሠላም ዘብ ለመሆን አበክረን እንሠራለን ሲሉም ተናግረዋል።

“የዛሬ ተመራቂ መሠረታዊ ወታደሮችም የሠራዊት ግንባታ አንድ አካል በመሆናችሁ ለሀገራችን ህልውና መረጋገጥ በተመደባችሁበት የሠራዊት ክፍል ግዳጃችሁን በጀግንነት እንድትወጡ አሳስባለሁ” ብለዋል።

የአዋሽ ቢሾላ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ ኮሎኔል መኮንን መንግስቴ በበኩላቸው መሠረታዊ ውትድርና እንድናሰለጥን ግዳጅ ከተሠጠን ጊዜ ጀምሮ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሰርተናል፤ ለስልጠናው ስኬት ባለድርሻ አካላትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል።

መሰረታዊ ወታደሮች በማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ የተሠጣቸውን የአካል ብቃትና የስነልቦና ግንባታ የወሰዱ፤ በወታደራዊ ቴክኒክ እና ታክቲክም የተካኑ መሆናቸውንም ኮሎኔል መኮንን ጨምረው ገልፀዋል።

የውትድርና ሙያ በአንድ በተከለለ ማሰልጠኛ ተቋም ብቻ የሚገደብ አይደለም ያሉት ኮሎኔል መኮንኑ፤ ተመራቂ መሠረታዊ ወታደሮች በሚሰማሩበት ግዳጅ እና በሚመደቡበት የጦር ክፍል አቅማቸውን ለማሳደግ ተግተው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በዕለቱ በስራ አፈፃፀማቸው አብላጫ ውጤት ላስመዘገቡ አሰልጣኞች የተለያዩ ሽልማቶች የተበረከቱ ሲሆን፤ ለስልጠናው ስኬት ድጋፍ ላደረጉ ባለድርሻ አካላትም የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሠጥቷል።

በምረቃው መርሐ ግብር ላይ ጄነራል መኮንኖች፣ የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች እና አባገዳዎች እንዲሁም ከተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየበዓል ስጦታ ለጠነከረ ወዳጅነት!
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።