
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአፋር ክልል በሠመራ ከተማ ያዘጋጀው 13ኛው “ስለ ኢትዮጵያ” የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “ኢትዮጵያ አፋር ትሁን” ሲሉ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።
ብዙ ጊዜ ወደ ምዕራቡ ወደ ምሥራቁ ሄደን እውቀት ለመቅሰም የምናደርገውን ጥረት ያህል ወደ ማህበረሠባችን ገብተን ባህሉንና ያለውን ጥበብና እውቀት የመቅሰም ልምድ የለንም፤ አለን ከተባለም ለጥናት ብቻ ነው ሲሉ ነው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተናገሩት።
ኢትዮጵያ አፋር መሆን አለባት ያሉት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ከአፋሮች የምንማራቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ ሲሉ ዘርዝረው አብራርተዋል።
አፋሮች ታሪካቸውን በደንብ ያውቃሉ ለልጆቻቸውም በደንብ ይነግራሉ ይህ ትልቅ እሴት በመሆኑ ኢትዮጵያዊያንም እንደ አገር የኖርንበትን ድክመትና ጥንካሬ በደንብ ማወቅና እንደ አፋሮች ለልጆቻቸው ተገቢ በሆነ መልኩ ማስተላለፍ አለባቸው ብለዋል።
እየንዳንዱ ማህበረሰብ ለልጆቹ ታሪክ የሚነግርበት ባህል ሊኖረው ይገባል ሲሉም ነው የገለጹት።
አፋሮች ማንነታቸውን ከኢትዮጵያዊነት ጋር አጣጥመው ነው የሚኖሩት፤ “እንኳን እኛ ግመሎቻችን የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ያውቃሉ” የሚለው የአፋሮች ንግግር አፋርነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር ተጣጥሞ የቀጠለበት ጥበብ ነው ሲሉም ነው ዲያቆን ዳንኤል ያብራሩት።
በአፋር ክልል አፋርነትና ኢትዮጵያዊነት ተጣልቶ አያውቅም ይሄንን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊማረው ሊቀስመው የሚገባ ሀብት ነው ብለዋል ዲያቆን ዳንኤል።
በአፋር ትልቁ ባህል መረጃን ማንጠር መቻላቸው ነው፤ ኢትዮጵያም ይህንን ባህል ማድረግ አለባት፤ አፋሮች መረጃን እንዳለ አይለቁም አንጥረው ነው የሚለቁት፤ ኢትዮጵያም መረጃን የመለየትና የማንጠር ባህል ሊኖራት ይገባልም ነው ያሉት።
ከአፋር ልንማር የሚገባን አራተኛው ጉዳይ የመነጋገር ባህላቸውን ነውና ሁሉም በየደረጃው በየባህሉ የመነጋገርና መወሠን የመቻል ባህልን ማዳበር ያሥፈልጋል፤ በጋራ በመወሰን መመራት ከተቻለም አንድነትን ማምጣት ይቻላል የሚለው በመድረኩ ላይ የቀረበው ሌላው የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሃሳብ ነው።
በአፋር ሽማግሌ የጎሳ መሪ የሃይማኖት አባት ይደመጣል፤ መረጃ ሲመጣ ማነው ያለው ተብሎ ተጠይቆ ከእነዚህ አዋቂዎች ከመጣ ብቻ ተቀብሎ ይተላለፋል፤ ይተገበራል፤ ይህ እሴት በሀሰተኛ መረጃ ለምትታመሰው ኢትዮጵያ ትልቅ ትምህርት ነውና መቅሰም ይገባናል ብለዋል።
በሌላ ሃሳባቸውም እንደ ሰንደቅ አላማ ላሉ ትምዕርቶቻችን ክብር እንስጥ ያሉት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ለየአካቢዎቻችን መሪዎች፣ አዋቂዎች፣ ህግና ህጋዊ ተቋማት እንዲሁም መሰል ምልክቶቻችን ሁሉ ክብር መስጠት ይገባናል ይህንንም ከአፋሮች የምንማረው እውነታ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
ህገመንግሥታዊነት ትዕምርት ነው መከበር አለበት በህገ መንግሥቱ ውስጥ ችግር ካለ ያንን እንደ አፋሮች ባህል በመነጋገር መረጃን አንጥሮ በመለየት ማሻሻል ይቻላል ም ብለዋል።
ሌላው ከአፋር መማር ያለብን ጀግንነትን የመናገር የመዘከር ባህል ነው ያሉት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ በአፋ ጀግንነት ይነገራል ይዘከራል፤ ሰለዚህ የደረሰብን ክፉ ክፉውን ሣይሆን መልካሙን መንገር ለልጆቻችን ማሻገር ይገባናል ብለዋል።
በመጨረሻም ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “አሸንፈን ሠላምን አንድነትንና ልዕልናን ማምጣን እንድንችል ኢትዮጵያ አፋርን መሆን አለባት” ሲሉ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
እንደ ኢፕድ ዘገባ፤ በአሁኑ ወቅት በቀረቡት ጽሁፎች ላይ ተሳታፊዎች ሃሳባቸውን እየሰጡ ውይይት ተደርጎበታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!