
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ ከነበሩ ስዊዲናዊያን ቤተሰቦች ሁለት ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ የብራና የጽሑፍ ቅርሶች በዛሬው ዕለት ወደ ሀገር መመለሳቸውን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን አስታወቀ።
በ1950ዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው ይኖሩ ከነበሩ ሲውዲናውያን ቤተሰቦች አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ክርስትል ዌስትላንድ ሃርቡ ባለቤታቸው ከኢትዮጵያ ወደ ዴንማርክ ይዘውት የወጡትን፣ በጽሑፍ አጣጣሉ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተጻፈ አንድ የግዕዝ መዝሙረ ዳዊት እና አንድ የግእዝ መልክዓ-ማርያም የግል የጸሎት መጽሐፍ በራሳቸው ተነሣሽነት ለስዊዲሽ የወዳጅነት ማኅበር አስረክበዋል።
ከተቋቋመ 70 ዓመታን ያስቆጠረውን የስዊዲናዊያን የወዳጅነት ማኅበርን ላለፋት ስድስት ዓመታት በሊቀመንበርነት የሚመሩት ኢትዮጵያዊው ስዊዲናዊው ዶክተር ቢንያም ወንድሙ ራሳቸው ቅርሱን ወደ ሀገር በማምጣት ለኢትዮጵያ የቅርስ ባለሥልጣን አስረክበዋል።
ዛሬ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በተደረገው የቅርስ ርክክብ ሥነ-ሥርዓት የስዊዲናዊያን የወዳጅነት ማኅበር ሊቀመንበር በዶክተር ቢንያም ወንድሙ እና በኢትዮጵያ የቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረ•ፕ•ር) መካከል የቅርስ ርክክብ ተከናውኗል።
የኢትዮጵያ የቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው ከሀገር የወጡ ቅርሶች ለማስመለስ የተደረገውን ጥረቶችን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር፣ ባለፉት ዓመታት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ጋር በመተባባር በተለያዩ ጊዜ ከሀገር የወጡ ቅርሶችን በማስመለስ ረገድ የተሻለ እንቅስቃሴ እንደነበረ ጠቁመዋል።
ዘንድሮም ብሔራዊ ኮሚቴውን በማጠናከር የተሻለ የቅርስ ማስመለስ ሥራ እንዲያከናወኑ የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።
በዕለቱ በቅርሱ መመለስ በየደረጃው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት የእውቅና የምስክር ወረቀት የተበረከተላቸው መኾኑን ኢቢሲ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!