የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ያለምንም የፀጥታ ስጋት ለማክበር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናዎናቸውን ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡

93

ላልይበላ: ታኅሣሥ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአዳም የእዳ ደብዳቤ የተቀደደበት የክርስቶስ ኢየሱስ መወለድ እና የኢትዮጵያዊያን መናኒያን እና መንፈሳዊያን አድካሚ ጉዞ ያከተመበት የቅዱስ ላል ይበላ ልደት በደብረ ሮሃ በየዓመቱ በልዩ ድምቀት ይከበራል፡፡ እረኞች እያጨበጨቡ፤ መላእክት እያሸበሸቡ የተቀበሉት ሕፃኑን ክርስቶስ ኢየሱስ ዛሬም በየዓመቱ ልደቱን አስበው በምስጋና የሚያሳልፉት እልፍ ናቸው፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስን እና የቅዱስ ላል ይበላን የልደት በዓል በተለየ ድባብ የምታከብረው ደብረ ሮሃ የእግዚያብሔርን ቸርነት፤ የቅዱስ ላል ይበላን ጠቢብነት እያወሱ እና እያስታወሱ ቀኑን በተለየ ድምቀት ያሳልፋሉ፡፡ ከሀገሪቱ አራቱም አቅጣጫ የቻሉት በእግራቸው ያልቻሉት ደግሞ በትራንስፖርት ተጉዘው ላስታ ደብረ ሮሃ ቅዱስ ላል ይበላን እና አካባቢውን እየጎበኙ በቤተ ክርስቲያን እድሞ ስር እየተኙ በምስጋና ያሳልፉታል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት ኾኖ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ እና በኢትዮጵያ ለዓመታት የዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ያለፉት ሦስት ዓመታት የልደት በዓል አከባበርን ቀዝቃዛ አድርገውት አልፈዋል፡፡ አሁን በሀገሪቱ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ከግምት ውስጥ በማስገባት የዘንድሮውን የልደት በዓል በተለየ ሁኔታ ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ከቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መካከል አንዱ የላል ይበላ ከተማን እና የአካባቢውን ሰላም እና ጸጥታ በማስከበር እንግዶች እና ጎብኝዎች ያለምንም የጸጥታ ሥጋት በዓሉን በሰላም አክብረው እንዲመለሱ ማድረግ ነው ተብሏል፡፡ የላል ይበላ ከተማ አስተዳደር ሰላም እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ ታደሰ ወራሽ በተለይም ለአሚኮ እንደገለጹት በበዓሉ ሰሞን የከተማዋን እና አካባቢውን ሰላም በተለየ ሁኔታ ለመጠበቅ ከአንድ ወር ቀድሞ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጀመራቸውን ነግረውናል፡፡

የፀጥታ ሥራው ሕዝብን ያሳተፈ እና ወጣቶችን ያካተተ ነው ያሉት ኅላፊው በእስካሁኑ ቆይታ የጸጥታ ችግር ምልክቶች አልተስተዋሉም ብለዋል፡፡ ወጣቶች ከጸጥታ አካላት ጋር በትብብር ተልዕኮ ወስደው እየሠሩ መኾኑን ያወሱት ኅላፊው የተሰጣቸውን ሥምሪት በአግባቡ እየተወጡ ነውም ብለውናል፡፡

ምዕመናን እና ቱሪስቶቸ በዓሉን ያለምንም የፀጥታ ስጋት እንዲያከብሩ መልዕክት ያስተላለፉት ጽሕፈት ቤት ኅላፊው የተለየ ሁኔታ ሲያስተውሉ ለጸጥታ አካላት መረጃ በመስጠት እንዲተባበሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል በድምቀት ለሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት በቂ የጸጥታ ስምሪት ማከናወኑን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።
Next articleበዴንማርክ የነበሩ ጥንታዊ የግእዝ መድብሎች ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን አስታወቀ።